Monday, September 17, 2012

ተኣምር እንጠብቃለን እንጅ ይሄማ እንዴት?

ተኣምር እንጠብቃለን እንጅ ይሄማ እንዴት?

አዲስ አድማስ ጋዜጣ በእለተ ቅዳሜ መስከረም 5 እትሙ የፊት ለፊት ገፁ ላይ “እነ አህመዲን ጀማል ምክር ቤቱን ይቅርታ ጠየቁ” በሚል የዜና ርዕስ ስር “የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤቱ በደብዳቤዉ ላይ እየተወያየ ነው…” የሚለውን በማከል ዜና መስራቱን አስተውለናል፡፡
ስለዜናው ብዙ ማለት ቢቻልም አስገራሚነቱ አንድ የሚያደርገን መሆኑ አያከራክርም፡፡ ከ17ቱ ወኪሎቻችን ስምንቱ መታሰራቸውን ጨምሮ የዘገበዉ ይህ ጋዜጣ ይህንን ወሬ ለህዝብ በማድረስ ከመገናኛ ብዙሃን እስከ አሁን ቀዳሚዉና ብቸኛዉ ሳይሆን አልቀረም፡፡
ለዲሞክራሲ ስርዓት አስተዳደር መረጋገጥ እውን መሆን 21 አመታት በስልጣን ላይ የከረመ መንግስት ለሥርዓቱ ዘብ በመቆምና ቁርጠኝንቱን በማሳየት የስርዓቱ ምሰሶ የሆነውን የብዙህንን ድምጽ የማክበርና የማስከበር መርሕ በተግባር በማሳየት ህዝቡን ማስተማር ሲጠበቅበት በተቃራኒዉ ህዝብ የተሰማውን ቅሬታ ፍጹም በሰላማዊ መንገድ የማሰማት ሂደት ውጤታማ በሆነ መልኩ በማካሄድ ህዝብ መንግስትን እያስተማረ ይገኛል፡፡ ከዚህ ሂደት አንዱ ኮሚቴዎቻችንን የመረጥንበት ሂድት ይገኛል፡፡ ምንም እንከን የማይወጣለት ይህ አካሄድ ሌላ ስም ቢሰጠዉም መልካም ታሪክ አስመዝግቦ ራሳችንንም ያኮራ ሂደት እንዲኖረን፣ እስካሁንም ድረስ ዘላቂነቱን የጠበቀ እንዲሆን አስችሎታል አልሃምዱሊላህ፡፡
 ወኪሎቻችንን የመረጥንበት ሂደት እንከን አልባ መሆኑን 100 ፐርሰንት እርግጠኛ የሆንበትን ያክል እኛን በሂደቱ በመምራት፣ የሰጠናቸውን አደራና ኃላፊነት በመወጣት ተግባራቸውም ላይ እንዲሁ እርግጠኞች ነን፡፡ እነሱ ልጆቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ ጓደኞቻችን፣ አባቶቻችን ከምንም በላይ የሰላም አምባሳደር የእምነታችን አጋር ናቸው፡፡ ለእስር እስተዳረጉበት ጊዜ ድረስ የሰሩት ወንጀልም ሆነ ሕገ ወጥ ድርጊት የለም፡፡ በዚህች ዲሞክራሲ እንጭጭ በሆነባት፣ ነገሮች በአንዴ መልካቸው ተለውጦ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊፈሱ በሚችሉበት እና በተለያየ አመለካከት የተለያየ ፅንፍ ያለው የኅብረተሰብ ስብጥር ባለባት ምድር ውስጥ እየተኖረ የኮሚቴዎቻችን ሀሳብ ሙሉ ተደማጭነት አግኝቶ ሕዝቡን በሠላም መምራት መቻላቸው ምንኛ ብቃት ያላቸው መሆኑን ያስመሰክራል፡፡ ሕዝቡም በዚህ አጋጣሚ ታዛዥነቱን፣ ለሕግ የበላይነትና ለሠላም ዘብ ቋሚነቱን አረጋግጧል፡፡
ኮሚቴዎቻችን ለእስር ከተዳረጉ ወዲህ እርስ ብርሳቸው የሚጋጩና ቋሚነት የሌላቸው በርካታ መረጃዎች ለሕዝብ ጆሮ ይደርሳሉ፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ በወሬዎቹ ሳይደናገጥ እና ሳይረበሽ አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ለኮሚቴዎቻችን መልካሙን ሁሉ እንዲገጥማቸው ሌት ተቀን ዱዓ በማድረግ ከፊት ለፊቱ ያለውን ዋና ዓላማ ዳር ለማድረስ ሲተጋ ከርሟል፡፡ይህም በተጠናከረ መልኩ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ኮሚቴዎቻችን ከማንም አካል ጋር በማይገናኙበት ሁኔታ እንዲህ አሉ፣ እንዲህ መሆናቸው ተረጋገጠ… የሚሉ ወሬዎች ዛሬም እንደቀጠሉ ሆነው እነሆ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከላይ ያነሳነውን ወሬ አስነብቦናል፡፡ የዚህ ዜና ዓላማ ምን እንደሆነ በትክክል ሊያውቅ የሚችለው ዜናውን የሠራው አሊያም እንዲሰራ ያዘዘው አካል ቢሆንም የዜናው አስገራሚነት አንድ ነገር ሳይባል እንዳይታለፍ ያስገድዳል፡፡ ይኸውም “እነ አሕመዲን ጀማል ይቅርታ ጠየቁ” ከሚለው ጋር በተያያዘ ይቅርታ የተጠየቀው አካል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መሆኑ ነው፡፡ “…ተከሳሾቹ ለእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት የይቅርታ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ምንጮች ጠቆሙ”ይላል ዜናው ቃል በቃል፡፡ በተጨማሪም ዜናው “ተከሳሾቹ የሠራነው ሥራ ሥህተት በመሆኑ እንደገና በመወያየት ወደ ተሻለ እና አዲስ አሠራር እንድንመጣ እንፈልጋለን…” ፣ “አሕመዲን ጀማልን ጨምሮ በእስር በሚገኙት ሥምንት አባላት ፊርማ ደብዳቤው ለምክር ቤቱ እንደደረሰም ምንጮች ተናግረዋል፡፡” በማለት አክሎ ዘግቧል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ የሠጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ምንም እንከን እንዳልፈፀሙ የሚተማመንባቸው የሕዝብ ወኪሎች ይቅርታ የሚጠይቁበት ምክንያት ለሰሚው ግራ ሲሆን ይቅርታ የሚጠየቀው አካል ሕገ ወጡ እና በሙስና የተዘፈቀው የመጅሊሱ አመራር መሆኑ ነገሩን የማይፈታ እንቆቅልሽ ያደርገዋል፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ የሠራው ዜና ሊያስተላልፈው የፈለገው የራሱ መልዕክት ሲኖረው ይህ ዜና በሙስሊሙ ልብ ውስጥ የሚፈጥረውን ሥሜት ማዳመጥ አንዱ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ኮሚቴዎቻችንን እንወዳቸዋለን፣ እናከብራቸዋለን፣ የከፈሉትን ሁለንተናዊ መስዋዕትነት መቼም ቢሆን የምንረሳ አይደለንም፡፡ ኮሚቴዎቻችን በአንድ ወቅት የትግል መሪዎቻችን እና አጋሮቻችን ነበሩ፡፡ ኮሚቴዎቻችንን በማሠር የሕዝብ ተቃውሞ እንደሚያቆም የተነበየው አካል ሳይሰምርለት እነሱ ከታሠሩም በኋላ እስከ ዒድ አደባባይ ድረስ ተቃውሞው ቀጥሏል፡፡በዒድ አደባባይ የታየው ተቃወሞ የሙስሊሙ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢው ምላሽ እስካላገኘ ድረስ ሂደቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል አመላክቷል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ኮሚቴዎቻችን ትግሉን ሊመሩ ይቅርና በቤተሰቦቻቸው እንኳን በቅጡ ሊጎበኙ አልተቻለም፡፡
ማንም አካል ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ሕዝበ ሙስሊሙ ከያዘው የጠነከረ አቋም እንዲያፈገፍግ ለማድረግ ያለውን ቢል የኛ ዓላማ ትግላችንን በሠላማዊ መንገድ በመቀጠል ዳር ማድረስ ነው፡፡ ኮሚቴዎቻችን ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ በውል መረዳት ባልቻልንበት ሁኔታ እነሱን በማስመልከት የሚወጡ መግለጫዎችም ሆኑ ዜናዎች ከነሱ አንደበት እንደወጡ በማሰብ የግል አስተያየት መስጠት በጣም የሚቸግር ጉዳይ ይሆናል፡፡ የሆነውን ሁሉ እውነት ብለን የምንቀበለው አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ፈቃዱ ሆኖ እነሱን በአካል አግኝተናቸው የሚሉትን ሥንሠማቸው ብቻ ይሆናል-ኢንሻ አላህ፡፡
ከኛ የሚጠበቀው ሁሉን ነገር በተለመደው ትዕግስታችን እና ብስለታችን ከአላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ጋር በመሆን ወደ ፊትና ወደ ፊት መራመድ ብቻ ነው፡፡ አላህ ይርዳን፡፡

አላሁ አዕለም፡፡

No comments:

Post a Comment