Tuesday, September 18, 2012

ዕውን ያለ መስዋዕትነት ድል ይገኛልን?!

ዕውን ያለ መስዋዕትነት ድል ይገኛልን?!
- በነስሩዲን ዑስማን
ባለፈው ሳምንት ‹‹በሕግ ከለላ ሥር ይገኛሉ›› በሚባሉት የህዝበ ሙስሊሙ ተወካዮች፣ ዳዒዎች፣ ጋዜጠኞች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ላይ እየተፈፀሙ ያሉት ኢ ሰብዓዊ ተግባራት በ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› አማካይነት ይፋ በተደረጉ ማግስት የዋለውን ጁምዓ የአዲስ አበባ ሙስሊሞች አንዳችም ድምጽ ሳናሰማ አሳለፍነው! ምንም ዓይነት ወንጀል ባልሠሩ ወንድሞቻችን ላይ እየደረሰ ያለው አካላዊና ስነ ልቦናዊ ስቃይ እጅግ አስቆጥቶን፣ ትግሉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ከተስማማን በኋላ፣ ጥቂት ቆየት ብሎ ከአሚሮቻችን በተላለፈ መልዕክት መሠረት ምንም ዓይነት ተቃውሞ ላናደርግ (ድምጻችንን ላናሰማ) ወሰንን፡፡ …

የጠ/ ሚኒስትር መለስን ህልፈት ተከትሎ ተቋርጦ የቆየው መብትን የማስከበር እንቅስቃሴ በመላ አገሪቱ በሚገኙ መስጂዶች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከተወሰነ በኋላ የተቀለበሰው፣ ‹‹አንዳንድ ባለሥልጣኖች አሁን ያለውን የመንግሥት አመራር ክፍተት በመጠቀም ሁከት በማስነሳት ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሰዉን በገፍ ጭነው ለማጋዝ መመሪያ መስጠታቸው ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ሙስሊሙን ህብረተሰብ ሊደርሱ ከሚችሉ አላስፈላጊ ጉዳቶች ለመታደግ …›› በሚል ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ውሳኔ የተላለፈው፣ ማለትም ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የተቃውሞ ትዕይንት የተሰረዘው ‹‹ሹራ ተደርጎበት›› መሆኑ በአሚራችን ስለተነገረን የተቃውሞውን መሠረዝ ይሁን ብለናል፡፡ …
ሹራ ተደርጎበት የተላለፈው ውሳኔ በአሚራችን ሲነገረን ያለአንዳች ማመንታት መስማማታችን እጅግ ተገቢ እና የአጠቃላዩ ትግላችን ጠንካራ ጎን አንዱ መገለጫ መሆኑ አይካድም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ በአንድ በኩል የውሳኔው መነሻ (Premise)፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመነሻ ሐሳቡ ላይ ተመሥርተን የወሰድነው ድምጽን ያለማሰማት ውሳኔ፣ ቁልፍ ጥያቄዎችን አንስተን ውሳኔያችንን በጥንቃቄ እንድንገመግም የሚጋብዝ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ይህንን ማድረግ በግምገማችን ላይ ተመስርተን ቀጣይ ትግላችንን ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በተገናዘበ ጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ያስችለናል ብዬ አምናለሁ፡፡ …
መሠረታዊ ጥያቄዎች …
ለመነሻ አንድ አጠቃላይ ጥያቄ አንስቼ የግሌን አስተያየት ካከልሁበት በኋላ፣ በቀጣይነት ሌሎች ቁልፍ ጥያቄዎችን በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡
• በመጪው ጁሙዓ ዋዜማ ባለፈው ሳምንት ውሳኔያችንን ያስቀየረን ዓይነት ‹‹መመሪያ›› ከ‹አንዳንድ ባለሥልጣናት› የተላለፈ ስለመሆኑ በ‹‹ታማኝ ምንጭ›› ቢነገረን ምንድነው የምናደርገው?! ‹‹በገፍ ጭነው እንዳያግዙን፣ እንዳይደበድቡን›› ወዘተ. በሚል ዳግም ድምጻችንን ላለማሰማት መወሰን ይኖርብናልን?!
… በእኔ እምነት ይህንን የምናደርግ ከሆነ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ያካሄድነውን ሰላማዊ መብትን የማስከበር ትግል በፍርኃት እና በክህደት ብቻ ሳይሆን፣ በመታለልም ጭምር እንዳጠናቀቅነው ነው የሚቆጠረው፡፡ እንደኔ ከሆነ ባለፈው ጁሙዓ ዋዜማ ከታመነ ምንጭ የደረሰን መረጃ በደፈናው ተቃውሟችንን የመሰረዝ ምክንያት ከሚሆነን ይልቅ፣ መረጃውን ከግምት ያስገባ፣ ማለትም በመረጃው ላይ ተመስርቶ ህዝበ ሙስሊሙ ምን ማድረግ እንዳለበት እና ምንስ ማድረግ እንደሌለበት የሚጠቁም ልዩ የተቃውሞ ስልት ለመንደፍ ልንጠቀምበት ይገባ ነበር፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ፣ በደነደነ መሠረት ላይ የተጣለውን ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን ለማፋፋም ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል ብዬ የማምንባቸውን ቁልፍ ጥያቄዎች ላስከትል፡
• ያለ መስዋዕትነት ድል ይገኛል ብለን እናምናለን? …
• ቀድሞ ነገር መንግሥት ለምንድን ነው ኮሚቴዎቻችንን ያሠረው? …
• ኮሚቴዎቻችን … እየተፈፀመባቸው ያለውን ሕገ ወጥ እና ኢ ሰብአዊ ቅጣት በጽናት እየተሸከሙ ያሉት ለምንድን ነው? …
• በዕለተ ዒድ በአገሪቱ በርካታ ከተሞች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ባካሄዱት ደማቅ የተቃውሞ ትዕይንት በመጅሊስ ዙርያ የተነሱት ጥያቄዎች የመላው የአገሪቱ ሙስሊሞች የጋራ ጥያቄ መሆናቸውን በማያሻማ ሁኔታ ካስተጋቡ በኋላ፣ በመንግሥት በኩል ‹‹ጥያቄው የመላው ህዝበ ሙስሊም ጥያቄ ነው›› የሚል ግንዛቤ መወሰዱን የሚያመለክት አዎንታዊ እርምጃ አለን? …
• ከዒድ በኋላ ባለው ጊዜ ህዝበ ሙስሊሙ እውቅና የነፈገው ‹‹የዑለማ ምክር ቤት ተብዬ›› ለነሐሴ 21 አቅዶት የነበረውን ህዝብ አልቦ ‹ምርጫ› ጊዜውን [ለመስከረም 27] ከማዛወሩ በቀር፣ በተዋረድ ካሉ የመንግሥት አካላት ጋር በመተባበር ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አቋርጧልን? …
• ጥያቄው የመላው የአገሪቱ ሙስሊሞች እንደመሆኑና የችግሩ ዘላቂ መፍትኄም በመንግሥት እጅ ሆኖ ሳለ፣ መንግሥት የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን፣ ዳዒዎችን፣ ዱዓቶችን፣ ጋዜጠኞችንና የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን አስሮ ማቆየትን የመረጠው ለምንድን ነው?...
• መንግሥት በእስር ላይ ወደሚገኙት የኮሚቴው አባላት ሽማግሌ የሚልከው፣ ህዝበ ሙስሊሙ ላነሳቸው ከእምነት የመነጩ የመብት ጥያቄዎች መፍትኄ ለመሻት ነውን? … ከሆነ መጀመርያ ለምን ከእስር አይፈታቸውም?…
ሽምግልና፣ ይቅርታ እና እኩይ ቅድመ ሁኔታዎች
መንግሥት የኮሚቴውን አባላት፣ ዳዒዎችን፣ ዱዓቶችን፣ ሙስሊም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን እና ጋዜጠኞችን በአሸባሪነት ከስሶ፣ ‹‹ማስረጃዬን እስካጠናቅር ጊዜ ይሰጠኝ›› በሚል ‹‹ሕጋዊ ፌዝ›› ቀጠሮ ከማራዘሙ በተጓዳኝ፣ ታሳሪዎቹ የዋስትና መብት ተነፍገው በ‹‹ማቆያ ቤት›› እንዲከርሙ ካደረገ ይኸው ሁለት ወር ሊሞላ ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ‹‹በሽብርተኝነት ጠረጠርኳቸው›› የሚላቸውን እኒህኑ እስረኞች የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ ፈርመው እንዲወጡ ያግባቡለት ዘንድ ‹ሽማግሌዎችን› እየላከ እንደነበር ሰምተናል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? … መልሱ ግልጽ ነው፡፡ …መንግሥት ክስ የመሠረተበትን ጉዳይ የሚደግፍ በእጁ የማይገኝን የወንጀል ድርጊት ማስረጃ፣ አለወንጀላቸው አስሮና የዋስትና መብታቸውን ነፍጎ ከሚያሰቃያቸው ንፁሃን ዜጎች ‹‹የይቅርታ ደብዳቤ›› ላይ ማግኘት ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህ የግፍ ግፍ አይደለምን?! … የሚያሳዝነው፣ ‹በአንድ ድንጋይ [ሁለት ሳይሆን] ሦስት፣ ከተቻለም አራት ወፎችን መግደል የሚወደው ኢሕአዴግ በዚህም የማያቆም መሆኑ ነው፡፡ …
በእኔ እምነት ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ህዝበ ሙስሊሙ የሚወዳቸውን የኮሚቴ አባላት፣ ዳዒዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ሰብስቦ ሲያስር በዋነኛነት ዒላማ ያደረገው የሙስሊሙን ህዝብ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ እንጂ ግለሰቦቹን ብቻ አይደለም፡፡ በሽማግሌዎች አማላጅነት ‹‹የይቅርታ ጥያቄን›› መነሾ አድርጎ ኮሚቴዎቹን ከእስር ሊፈታ እንደሚችል ምልክት ሲያሳይም፣ በዋነኛነት ዒላማ ያደረገው የእነርሱን ከእስር ነፃ መውጣት ሳይሆን፣ የሙስሊሙን የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ ማኮላሸትን እንደሆነ ልንጠራጠር አይገባም፡፡ ይህንን መሠሪ የፖለቲካ ድራማ የሚሠራባት ቁልፍ መሣርያው ደግሞ ኮሚቴዎቻችን እንዲፈርሙለት የሚሻት ‹‹የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ›› ናት፡፡
በቅንጅቶች ላይ እና በድጋሚ የምህረት ጥያቄዋ ጊዜ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ እንዳደረገው፣ ‹‹የይቅርታ ደብዳቤውን›› የሚያረቅቀው ራሱ ‹‹ይቅርታ ጠይቁኝ›› ባዩ ኢሕአዴግ/መንግሥት ነው፡፡ የይቅርታ ደብዳቤው በሙስሊሙ ኅብረተሰብ መብትን የማስከበር ትግል ላይ የሚኖረውን አንድምታ የሚወስነው ይዘቱ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በእስር ላይ የሚገኙት ኮሚቴዎች ይቅርታ ጠይቀው እንዲወጡ ይፈልጋል ሲባል ከመስማት ያለፈ ምን የሚል ሐሳብ የሠፈረበት የይቅርታ ደብዳቤ እንዲፈርሙለት እንደፈለገ አናውቅም፡፡ በዚህ የይቅርታ ጥያቄ ጨዋታ ከገፋበትና የይቅርታ ደብዳቤውን እራሱ የሚያረቅቀው ከሆነ ግን፣ የደብዳቤው ይዘት የኮሚቴውን አባላት እና ሌሎቹንም እስረኞች ከኢስላማዊ እንቅስቃሴ ከማራቅ ባሻገር፣ በቀጣይነት የሙስሊሙን ህዝብ የመብት እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ያስችሉኛል ብሎ በሚያስባቸው መሠሪ ሐተታዎች እንደሚቃኘው ልንጠራጠር አንችልም፡፡ … የቅንጅት አመራሮች በ‹‹ምህረት›› በተፈቱ ጊዜ፣ እንዲሁም የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትኅ ፓርቲ ሊቀ መንበር የነበረችው ብርቱካን ድኅረ ምህረት ዳግም ለወህኒ ከተዳረገች በኋላ፣ ዳግም ምህረት ለመጠየቅ አቀረበችው የተባለውን ‹‹የምህረት መጠየቂያ ደብዳቤ›› ይዘት የሚያስታውስ ሰው፣ ለኢሕአዴግ ‹‹የምህረት መጠየቂያ ደብዳቤ›› የምህረት መጠየቂያ ደብዳቤ ብቻ እንዳልሆነ መገንዘብ አይገደውም፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት ወንድሞቻችን ከዚህ በላይ በጠቀስኳቸው ነጥቦች መንፈስ የተቃኘን የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ ይፈርማሉ ብዬ አላምንም፡፡ ሰሞኑን ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› ይፋ እንዳደረገው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በእስር ላይ የሚገኙት ወንድሞቻችን ለአስከፊ የማሰቃየት ቅጣት እየተዳረጉ ያሉት በሌላ ሳይሆን የሙስሊሙን ህዝብ ከእምነት የመነጨ የመብት ጥያቄ ለማኮላሸት የታለመ የይቅርታ ደብዳቤን ለመፈረም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ያነሳቸው የመብት ጥያቄዎች የእነርሱም ጥያቄዎች ቢሆኑም፣ ከእኛ በተለየ ዛሬ እነርሱ ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው ለእስር የተዳረጉት፣ ኢ ሰብአዊ ድብደባና ቅጣት እየተሸከሙ ያሉት፣ እኛው መርጠን ስለወከልናቸው እና የመላውን ሙስሊም ህዝብ ጥያቄ ከነፍሳቸው አብልጠው መስዋዕትነት ሊከፍሉለት ራሳቸውን ስላዘጋጁ ነው፡፡ እነርሱ ቃላቸውን አላጠፉም፡፡ … እነርሱ የጣልንባቸውን እምነት አላጓደሉም፡፡ … በእርግጥም እነርሱ ስለ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የመጻዒ ዘመን ዕጣ ታላቅ መስዋዕትነትን እየከፈሉ ናቸው፡፡ … ‹‹ጀግንነት›› ማለት ከቶ ከዚህ የተለየ ትርጉም አለውን?! …
‹‹እኛስ?!›› ብለን ራሳችንን እንጠይቅ እስቲ፡፡ ‹‹ምን ስንሰራ ከረምን?!›› … ‹‹አሁንስ ምን እየሰራን ነው?!›› … የጠ/ ሚኒስትሩን ህልፈት መነሾ አድርገን ያቋረጥነውን ሰላማዊ ትግል፣ ምናልባትም ‹‹በእነ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሐቅ ሊጀመር ነው›› ለተባለው ‹‹ሽምግልና›› ጊዜ ለመስጠት አስበን ይበልጥ አቀዛቀዝነው፡፡ … እውን ግን ኢሕአዴግ ከ‹‹ሽምግልና›› ሒደት ፖለቲካዊ ድልን እንጂ እርቅን ያልማል ብለን ማሰባችን ትክክል ነውን?! …
… እነሆ የእነፕሮፌሰር ኤፍሬም የሽምግልና ጥረት መሰናከሉንም ሰማን፡፡ እውን ግን የሽምግልና ጥረቱ የተጨናገፈው አንዳንድ ወንድሞች እንደጻፉት ‹‹ራሳቸዉን "የህዝብ ደኅንነት" ነን ብለዉ በሚጠሩ ክፍሎች እና በሕገ-ወጡ መጅሊስ›› አማካይነት ነውን?! …እውን እነፕ/ር ኤፍሬም የሽምግልና ጥረት የሚጀምሩት ተራ የመንግሥት ባለሟሎችን እና ራሱ መንግሥት በሙስሊሙ ህዝብ አናት ላይ ያስቀመጣቸውን የ‹‹መንግጅሊስ›› ካድሬዎች እየተለማመጡ ነው ተብሎ ይታሰባልን?! … እኔ አይመስለኝም፡፡ በእኔ እምነት የችግሩ ዋነኛ ምንጭ ሁሌም ማሸነፍን እና ማሸነፍን ብቻ የሚፈልገው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ነው፡፡ በእኔ እምነት የችግሩ ምንጭ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በሽማግሌዎች አማካይነት በእስር ላይ ለሚገኙት ኮሚቴዎቻችን የሚያቀርባቸው የህዝበ ሙስሊሙን የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ ድባቅ ለመምታት ያለሙ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ … በእስር ላይ የሚገኙት ወንድሞቻችን ለአስከፊ ስቃይ እና እንግልት እየተዳረጉ ያሉት እኒህን ቅድመ ሁኔታዎች መቀበል በሙስሊሙ ህዝብ ከእምነት የመነጨ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረውን አስከፊ አንድምታ በመረዳታቸው ይመስለኛል፡፡ ይህ ዕውን እንዳይሆን የሚጠይቀውን ማንኛውም መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው፡፡
በአንጻሩ እኛ ከዛሬ ነገ ኢሕአዴግ ሆዱ ይራራል፣ ወይም ህዝባዊነት ይሰማዋል በሚል የዋህ ተስፋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አድማሱ እየሰፋና እየጠነከረ የመጣውን ሰላማዊ ትግል እያቀዛቀዝነው እንገኛለን፡፡ የሚያሳዝነው እኛ ቀና ቀናውን በማሰብ ትግላችንን ስናቀዛቅዝ፣ ኢሕአዴግ ‹‹ሁሌም አሸናፊ›› የመሆን ክፉ በሽታው የሚያገረሽበት መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ከእምነታችን የመነጩ የመብት ጥያቄዎቻችን ተገቢ ምላሽ ያገኙ ዘንድ ሰላማዊ ህዝባዊ ትግላችንን አጠናክረን ከመቀጠል ውጪ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ከ‹‹ተዓማኒ ምንጮች›› የሚገኙ መረጃዎችን ለተቃውሟችን ስልት ግብዓት ልናደርጋቸው እንጂ፣ ከትግላችን የማፈግፈጊያ ምክንያት ልናደርጋቸው አይገባም፡፡ በኢሕአዴግ ላይ ጫና ማሳደር የምንችለው ትግላችንን በከፍተኛ የዓላማ ጽናት፣ በእስር ላይ እንደሚገኙት ወንድሞቻችን ራሳችንን ለመስዋዕትነት በማዘጋጀት ይበልጥ አጠናክረን በማፋፋም እንጂ፣ ጮሌው ኢሕአዴግ በ‹‹ተዓማኒ ምንጮች›› አማካይነት እንዲደርሱን በሚያደርጋቸው መረጃዎች በመዘናጋት አይደለም፡፡
ሰላማዊነት፣ ጽናት እና መስዋዕትነት …


የእኛ ኃይል ያለው የአላህን እገዛ አጥብቀን ከመሻት ጋር እየተደበደብንም፣ እየተገደልንም ሰላማዊ ትግላችንን በጽናት በመቀጠላችን ላይ ነው፡፡ ያለ መስዋዕትነት ድል ይገኛል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡

… ዴሞክራሲ ሲያልፍ የማይነካካቸው የታዳጊ አገራት የፖለቲካ መሪዎች የህዝብን ድምፅ ለማፈን ግድያን ጨምሮ ማንኛውንም መንገድ ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን ለመግደል ሰበብ ይፈልጋሉ፡፡ ያም ሰበብ ሁከት ነው፡፡ የእንቅስቃሴውን ሰላማዊነት በአስተማማኝ መልኩ ዕውን ለማድረግ የቻለ የህዝብ ንቅናቄ እንዲህ ያሉ እኩይ ፖለቲከኞችን የመግደያ ሰበብ ያሳጣቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ የራሳቸውን ስውር ኃይል በማስረግ ሁከት ለመቀስቀስ ይተጋሉ፡፡ …ሁከት የመቀስቀስ ሤራቸው ከተሳካ ያንን አስታክከው መላውን ህዝብ የሚያስደነግጥ ህይወት የማጥፋትና የብዙዎችን አካል የማጉደል ጭካኔ የተመላበት እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ ከዚያም ለጠፋው ህይወት የሰላማዊውን እንቅስቃሴ መሪዎች ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ ይህንን ወራዳ ፖለቲካዊ ሸፍጥ ለኢትዮጵያዊያን መንገር ‹‹ለቀባሪው ማርዳት…›› ነው የሚሆነው፡፡ በ1987 በአንዋር መስጂድ 11 ሰዎች የተገደሉበትን፣ እንዲሁም በ1997 በአዲስ አበባ 193 ንፁኃን ዜጎች የተገደሉበትን ሁኔታ የማያውቅ አለ ተብሎ አይታሰብም፡፡ የመንግሥት ደኅንነቶች እስካሁን በእንዲህ ያሉ ፖለቲካዊ ሸፍጦች የህዝበ ሙስሊሙን የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ ለማሰናከል ያደረጓቸው ጥረቶች አልተሳኩም፡፡ በአላህ እገዛ ወደፊትም አይሳኩም፡፡ ኢንሻአላህ፣ ሰላማዊው ትግላችን ምንጊዜም ሰላማዊ ሆኖ፣ ነገር ግን ይበልጥ ተጠናክሮ በመላ አገሪቱ ይቀጥላል፤ ይቀጣጠላል፡፡

በመጨረሻም፣ አጠናክረን በምንቀጥለው ሰላማዊ ትግል ውስጥ መላውን ሙስሊም ማኅበረሰብ ማነቃነቅ እጅግ ወሳኝ መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ በእስር ላይ የሚገኙ ወንድሞቻችን ስለ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መብት እጅግ ከባዱን መስዋዕትነት እየከፈሉ ባለበት በአሁኑ ሰአት፣ በፍፁም ዝምታ የምናሳልፈው እያንዳንዱ ቀን ሊያሳምመን ይገባል፡፡ ሐቅን ይዘን፣ በእምነታችን ላይ የሚሠራ ግዙፍ ሸፍጥን የምንፈቅድበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ‹‹አላህ ሆይ! ተበድለናልና እርዳን›› እያልን ወደ ኃያሉ ጌታ በፍፁም መተናነስ እናለቅሳለን፡፡ ኢንሻአላህ፣ አዛኙ ጌታችን ልመናችንን ይሰማናል፡፡ ‹‹መብታችን ይከበር!›› ስንልም ወደ መንግሥታችን እንጮሃለን፡፡ በጩኸታችን ብርታት፣ ለመስዋዕትነት በሚኖረን ዝግጁነት እና በጽናታችን ኢንሻአላህ መንግሥት መብታችንን ሊያከብር ይገደዳል፡፡ አላህ ከእኛ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment