(ደረጀ ሀብተወልድ-ሆላንድ) Source Facebook
የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ እና ሊፈነዳ የደረሰ ቂም እንዳለ በስፋት ይወራል። እርግጥ ነው፤ ባለፉት ዓመታት በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለይም በህወሀት እና በብአዴን መካከል ተዳፍነው የቆዩት የቂም እሳቶች በገሀድ የሚነድዱበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል።ስፍር ቁጥር ከሌላቸው የነ አቶ በረከት እና የህወሀቶች ቁርሾዎች መካከል ለዛሬ አንዱን እንመልከት።
በህወሀት ውስጥ በነ ስዬ እና በነ መለስ መካከል የተፈጠረው ክፍፍል በአቶ መለስ ቡድን አሸናፊነት በተጠናቀቀ ማግስት በክፍፍሉ ወቅት ለአቶ መለስ ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩት ብአዴናውያን ፤ከአለቃቸው- ቱባ ቱባውን ስልጣን “ጀባ” መባላቸው ይታወሳል። ኢትኦጵ መፅሔት በወቅቱ የቡሔን በዓል አስታክኮ በፊት ገፁ ላይ ያወጣው ካርቱን እስካሁን ትዝ ይለኛል።
አቶ መለስ በብአዴኖች ተከበው መሀል ላይ ቁጭ ብለዋል። አዲሱ ለገሰ ፦”ሆያሆዬ “እያሉ ያወራርዳሉ። እነ በረከት “ሆ!” እያሉ ተሰጥኦውን ይመልሳሉ።መለስ እጃቸውን የስልጣን ሙልሙል ወደያዘው ጆንያ እየሰደዱ ሹመት የተፃፈበትን ሙልሙል ያድሏቸዋል።
አዎ! ያኔ ሥልጣን እንደ ሙሉሙል ዳቦ ለብአዴኖች ታደለ፦
አቶ አዲሱ ለገሰ-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የገጠር ልማት ሚኒስትር፣ (በሥራቸው ወደ አምስት የሚጠጉ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችን ይቆጣጠራሉ) አቶ ተፈራ ዋልዋ-የ አቅም ግንባታ ሚኒስትር ፣(በሥራቸው ወደ ስድስት የሚጠጉ የሚኒስቴርና ባለሥልጣን መስሪያ ቤቶችን ይቆጣጠራሉ) አቶ በረከት ስምዖን- የማስታወቂያ ሚኒስትር፣ አቶ ከበደ ታደሰ-የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ የቀድሞዋ ባለቤታቸው እና የአሁኗ የህንድ አምባሳደር ወይዘሮ ገነት ዘውዴ-የትምህርት ሚኒስትር…..እየተባለ ሹመት በብአዴን ሰፈር በሽ በሽ ሆነ። ብአዴኖችም፤በዚያው ሰሞን የአሸናፊዎች አሸናፊን ዋንጫ አንስቶ ከነበረው የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጋር ደስታቸው ገጠመና፦ “እንደተመኛት አገኘናት” እያሉ ጨፈሩ፤ደነሱ።
በብአዴን ሰፈር ዕልልታው በቀለጠበት በዚያ ወቅት፤ በአንፃሩ በህወሀት አካባቢ ኩርፊያና እነሱ ራሳቸው እንደሚሉት፦ “መንገጫገጭ” በዝቶ ነበር።
በዚያው ሰሞን በተካሄደ አንድ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ታዲያ፤ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት(ማለትም አዲስ ዘመን፣ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በሬሳ፣ አልዓለም..) ተጠሪነታቸው ለአዲሱ ማስታወቂያ ሚኒስትር እንዲሆን፤ በሌላ አገላለፅ አቶ በረከት እነዚህን ሚዲያዎች በቦርድ ሰብሳቢነት እንዲመሩ፤ የወቅቱ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሪት ነፃነት አስፋው ደግሞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን በቦርድ ሰብሳቢነት እንዲመሩ የሚጠይቅ የሹመት ፕሮፖዛል በምክር ቤቱ የባህልና መገናኛ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት ለፓርላማው ይቀርባል። እንደተለመደው የኢህአዴግ አባላት ሃሳቡን እየደገፉ፤ተቃዋሚዎች ደግሞ እየተቃወሙ ውይይቱ ቀጠለ….
…በመሀከል ግን አንድ ያልተጠበቀ ሀሳብ- ካልተጠበቁ ሰው ተሰነዘረ።የቤቱ አጠቃላይ ድባብ ከመቅፅበት ተለወጠ…አዎ! አንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣን እጃቸውን በማውጣት በፕሮፖዛሉ ላይ ከፍ ያለ ተቃውሞ ማቅረባቸው፤ የውይይቱን መንፈስ ፈፅሞ ወዳልተጠበቀ መንገድ መራው።
ባለሥልጣኑ በቁጣ ድምጽ ተቃውማቸውን ቀጠሉ፦”….በፍፁም! በፍፁም! ተቀባይነት የሌለው ፕሮፖዛል ነው!አስፈፃሚው አካል በሚመራቸው መስሪያ ቤቶች የቦርድ ሰብሳቢ ይሁን ማለት፤አፈናን ማጠናከርና ራሱ ከተጠያቂነት እንዲያመልጥ መንገድ ማመቻቸት ነው…” ቁጣቸው እየጨመረ መጣ፦ “… ሰሞኑን የ ኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅን ወይዘሪት ሰሎሜ ታደሰን አግኝቻታለሁ።አቶ በረከት የማስታወቂያ ሚኒስትር ሆኖ ከተሾመ በሁዋላ አሠራራቸው ነፃነት ማጣቱን ነው የነገረችኝ…”
“…አቶ በረከት ገና በሹመቱ ማግስት ነባሩን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ህንፃ በመልቀቅ ቢሮውን ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 9ኛ ፎቅ አዛውሮታል።ከቅርብ ሆኜ ሁሉን ካልተቆጣጠርኩ ለማለትና ነፃነት ለማሳጣት ነው ይህን ያደረገው። እሱን ዝም ስንል ይባስ ብሎ አሁን ደግሞ በሥሩ የሚገኙ መስሪያ ቤቶችን በቦርድ ሰብሳቢነት ይምራ የሚል ኢ-ዲሞክራሲያዊ የሹመት ሰነድ ቀርቦልናል።ይህ ፈፅሞ ሊፀድቅ ቀርቶ ሊታሰብ የማይገባ ነው። ስለዚህ ይህ ምክር ቤት ይህን ፕሮፖዛል ሊያፀድቀው አይገባም!” አመሰግናለሁ!”
በቤቱ ውስጥ የፀጥታ ድባብ ሰፈነ። ተናጋሪው በስብሰባው ላይ ከነበሩት ከፍተኛ የኢህአዴግ ሹመኞች ዋነኛው በመሆናቸው፤ ለተባሉት ነገር በሙሉ እጅ ማውጣት የለመዱት የኢህአዴግ “እጅ ሥራዎች” ማለትም የፓርላማ አባላቱ ግራ ተጋቡ።አለቃቸው አቶ በረከት በሌሉበት የሹመት ፕሮፖዛሉን አቅርበው ያፀድቁ ዘንድ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸው የመጡት የባህልና መገናኛ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አህመድ ሀሰን በበኩላቸው መድረኩ ላይ እንደወጡ ዐይናቸው ፈጦ ቀረ። ነገሩ አላምር ያላቸው ምክትላቸው አቶ አማኑኤል አብርሐም ወደ መድረኩ በመውጣት የተሰጣቸውን የቤት ሥራ በድል ለማጠናቀቅ የተቻላቸውን ያህል ጥረት ቢያደርጉም፤ የሹመቱን ኢ-ዲሞክራሲያዊ አለመሆን ማስረዳት አልቻሉም።ድምፅ ሳይኖረው አይድል ሊወዳደር እንደመጣ ጎረምሳ በደፈናው ነው ድርቅ ያለ ሙከራ ያደረጉት። ውጤቱም፦”ለዛሬው አልተሳካም” የሚል ሆነ። ተንደርድረው ሲወጡ “ታሪክ ሊሠሩ ነው” የተባሉት አቶ አማኑኤል ፤እንደ አቶ አሕመድ ሁሉ ዐይናቸውን አፍጥጠው ቀሩ። የድሮው እረኛ ስንኝ ጆሮዬ ላይ አንቃጨለብኝ፦
ዳገት ዳገት ስሄድ አገኘሁ ሚዳቆ፣
ጅራቷን ብይዛት ዐይኗ ፍጥጥ አለ።
አዎ! በስተመጨረሻም ሁሉም የኢህአዴግ አባላት፤ እጃቸውን ተቃውሞ ላቀረቡት ባለስልጣን ሰጡ።ፓርላማው የአቶ በረከትን ሹመት ውድቅ አደረገ።የአቶ በረከትን የቦርድ ሰብሳቢነት ሹመት አጠንክረው በመቃወም ለአንድ ጊዜም ቢሆን ውድቅ እንዲሆን ያስደረጉት እኚህ ሰው፤ በወቅቱ የመንግስት ቃል-አቀባይና የፓርላማው የመከላከያና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ቋሚ ሰብሳቢ የነበሩት የህወሀቱ አቶ ሀይለ-ኪሮስ ገሠሰ ናቸው።
በወቅቱ ውስጥ አዋቂዎች አቶ ሀይለ-ኪሮስ የአቶ በረከትን የቦርድ ሰብሳቢነት ያን ያህል ርቀት ሄደው የተቃወሙት፤ ሲጠብቁት የነበረውን የማስታወቂያ ሚኒስትርነት ስልጣን ስለወሰዱባቸው ነው ቢሉም፤ለመቃወም የሰነዘሩዋቸው ሃሳቦች ግን “ሎጂካል “ ነበሩ።
እናም… በስብሰባው መጨረሻ እንደተለመደው አፈ-ጉባኤው ፦”የሹመቱን ፕሮፖዛል የምትደግፉ..” በማለት ቤቱን ጠየቁ።…. አንድም እጅ አልታየም-አንድስ እንኳ።
“እሽ የምትቃወሙ…”ሲሉ፤ ተቃዋሚዎች በድል አድራጊነት፤ኢህአዴጋውያኑ ደግሞ አቶ ሀይለ-ኪሮስን ተከትለው በአንድ ላይ እጃቸውን አወጡ።
ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ተቃዋሚዎችና የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ተመሣሳይ አቋም ያንፀባረቁበት፤ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ሃሳብ-በራሱ ሰው ውድቅ የሆነበት ታሪካዊ ቀን።
በነገሩ እጅግ የተደነቀው ይህ ፀሀፊ፤ሁኔታውን በወቅቱ ይሠራበት በነበረው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፦” ወደ ዲሞክራሲ አቡጊዳ ልንገባ ይሆን?” በሚል ርዕስ ለህትመት አብቃው።
ዳሩ ምን ያደርጋል?
በቀጣዩ ሣምንት የፓርላማው ስብሰባ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው፤ ይሄው በሁሉም የምክር ቤት አባላት ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ የተቋጨው የአቶ በረከት የቦርድ ሰብሳቢነት ሹመት ጉዳይ ሆነ።
ሁኔታው የልጆች ዕቃ ዕቃ የሆነባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፤በፓርላማው ውሳኔ የፀደቀን አጀንዳ ቆፍሮ በማውጣት እንደገና ለውይይት እንዲቀርብ የተደረገበት አሠራር ሊገባቸው ስላልቻለ ስብሰባውን እንደሚቃወሙ ቢገልፁም፤ የኢህአዴግ ዋነኞቹ ሹመኞች፦” እኛው የሠራነው ፓርላማ የኛን ሃሳብ ውድቅ አድርጎ የታባቱ ሊገባ?” በሚል መንፈስ እንደገና ታጥቀው ስለመጡ፤”የምን ህግ?” በሚመስል አመለካከት ስብሰባው እንዲጀመር አስደረጉ።በሌላ አገላለፅ የአቶ መለስ ቅኔ ተመዘዘ ፦
“ለጨዋታ ታህል-ሣሳያት መንገዱን፣
እሷ የምር አርጋው-ካወጣችው ጉዱን፣
ህጉን አዳፍኑልኝ-አስፉና ጉድጓዱን” የሚለው።
እናም ”… በአንድ ሣምንት ውስጥ ፤ሳይጨመርበት፤ ሳይቀነስበት ያው የሹመት ሰነድ በተመሣሳይ ሰዎች እንደገና ለዛው ምክር ቤት ቀረበ። በጣም በሚያስገርም ፍጥነት የድጋፍ ሀሳቦች ከኢህአዴጋውያኑ የፓርላማ አባላት መጉረፍ ጀመሩ…
”…ተገቢ የሆነ፣ተጠያቂነትን የሚያጠናክር…ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ “ወዘተ እየተባለ ያው ሰነድ መወደሱን፣መሞገሱን፣መሞካሸቱን ቀጠለ።
ግን…ግን እዚህ ላይ.…ሹመቱን በመደገፍ የመጀመሪያው ተናጋሪ የሆኑት ማን ይመስሏችሁዋል?
ብዙ አትመራመሩ።ባለፈው ሣምንት ፕሮፓዛሉን ወድቅ እስከማስደረግ ድረስ ጠንካራ የተቃውሞ አርበኛ ሆነው የታዩት አቶ ሀይለ-ኪሮስ ገሠሰ ናቸው።ልብ በሉ! አቶ ሀይለ ኪሮስ“ኮከብ ተጨዋች” ተብለው ከተመረጡ ገና አንድ ሳምንት አላለፋቸውም። ባለፈው ሣምንት ፦”አፋኝና ጨቋኝ” ያሉትን ፕሮፖዛል፤ ነው ዛሬ “ዲሞክራሲያዊ” ያሉት። ከጥቂት ቀናት በፊት ውድቅ እንዲሆን ሽንጣቸውን ይዘው የሞገቱትን ሀሳብ ነው፤ ዛሬ ይፀድቅ ዘንድ ቀበቷቸውን አጥብቀው እየተማፀኑ ያሉት።
ነገሩ፤ በሰዓታት ልዩነት ነጩን ጥቁር፤ እውነቱን ሐሰት ማለት ለለመዱት ለኢህአዴግ መሪዎች፣ ለካድሬዎቻቸውና ለሆደ-ትላልቅ ደጋፊዎቻቸው ምንም ላይመስል ይችላል-“የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ!” በሚል ብሂል ላደግነው ኢትዮጵያውያን ግን ይህን ማየትና መስማት እጅግ ከባድ ህመም ነው።አዎ!የጥላሁን ገሠሰን፦” ቃልሽ አይለወጥ እባክሽን..”፤ለመደነስ ያህል ሳይሆን ከልባችን እየሰማን ያደግን ኢትዮጵያውያን፤ለስምም ቢሆን ”የአገሪቷ ትልቁ የሥልጣን አካል ነው” በሚባል ፓርላማ ደረጃ የዚህ ዓይነት “በቃል መጨማለቅን” ስናይ፤ እንዴት ጤንነት ሊሰማን ይችላል?
አዎ! ከቀናት በፊት አቶ ሀይለኪሮስን ተከትለው የሹመት ፕሮፖዛሉን ውድቅ ያደረጉ ጭራሮ እጆች፤ዛሬም እርሳቸውን ተከትለው ሹመቱን ሊያፀድቁ ብቅ ብቅ ብለዋል። እንደኔ በቅርበት ለተከታተለው ነገሩ፦”አጃኢብ!”የሚያሰኝ ነው። መሥሪያ ቁሣቁሳቸው ችግር ያለበት ለወንበርና ጠረጴዛ የተመረጡ እንጨቶች እንኳ አላግባብ ሲመቱ፤ከአናፂያቸው ፈቃድ ውጭ ሢሰነጠቁና በራሳቸው ፍላጎት ወደ ተለየ አቅጣጫ ሲሄዱ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ- የኢህአዴግ አባላት ከግዑዝ እንጨት ያነሱበትና በራሳቸው ሀሳብ መሄድ ያልቻሉበት ምሥጢር ግን ሊገባኝ አልቻለም።
በስተመጨረሻም; ጉደኛው ፓርላማ ውድቅ አድርጎት የነበረውን የነ አቶ በረከት ሹመት አጽድቆ ስብሰባው ተጠናቀቀ። መቅረፀ-ድምፄን እንዳነገብኩ ከፎቅ ወደ ምድር ሮጬ በመውረድ መውጫ በሩ ላይ ቆምኩ። ከስብሰባው አዳራሽ ከሚወጡት የፓርላማ አባላት መካከል አንድ ሰው እየጠበኩ ነው። ሰውዬው ጓደኞቻቸውን ተሰናብተው ወደ መኪናቸው ሲያመሩ ተመለከትኳቸውና በፍጥነት ደረስኩባቸው፦
“ጤና ይስጥልኝ አቶ ሀይለኪሮስ፤” አልኳቸው።
“ለቃለ-ምልልስ ከሆነ ሰዓት የለኝም፤ እቸኩላለሁ”አሉኝ።
“ረዥም አይደለም፤ ባለፈው ሳምንት የተቃወሙትን የሹመት ፕሮፖዛል እንዴት ዛሬ ደገፉት? የሚለውን ብቻ እንዲመልሱልኝ ነው”
“ከየትኛው ጋዜጣ ነህ?” በማለት ጠየቁኝ
“ከአዲስ አድማስ” አልኳቸው።
ትንሽ እንደማቅማማት ካሉ በሁዋላ፦“ እህ…ባለፈው ሣምንት ያላየሁዋቸው አንዳንድ ነጥቦች ነበሩ፤ በሁዋላ ግን ረጋ ብዬ ሰነዱን ሳየው ተገቢና ዲሞክራሲያዊ ፕሮፖዛል እንደሆነ ተረዳሁ፤ስለዚህም ደገፍኩት” በማለት በአጭሩ መለሱልኝ-የመኪናቸውን በር ከፍተው ወደ ውስጥ እየገቡ።
“እነዚያን ነጥቦች ሊገልፁልኝ ይችላሉ?”
አልመለሱልኝም።መኪናዋ የፓርላማውን ቅጥር ለቅቃ ቁልቁል ሸመጠጠች…
እኔም ቀጣይ ዘገባዬን፦”አቡጊዳ ወይስ ሀሁ?” በሚል ርዕስ ለአንባቢዎቼ አቀረብኩ። የአቶ በረከት ሹመት ውድቅ ተደርጎ የነበረበት ያ ታሪካዊ ቀንም በጋዜጦች፦”ፓርላማው በስህተት ዲሞክራሲያዊ ሆኖ የዋለበት ቀን “ተባለ።
* * *
ይህ
ሁሉ ከሆነ በሁዋላ ከውስጥ ምንጮቼ እንዳረጋገጥኩት፤አቶ ሀይለኪሮስ -የአቶ በረከትን ሹመት ውድቅ ባደረጉ ማግስት፤
ከአቶ መለስ ያን ያህል ርቀት የሚያስኬድ ”ሊቸንሳ” ያገኛሉ ብለው ባልጠበቋቸው በአዲሱ አለቃቸው( ማለትም
በራሳቸው በአቶ በረከት ) ክፉኛ ተገምግመው ኖሯል።ግምገማው የተደረገውም፤ ፓርላማው ፊት ለፊት ባለው የኢህአዴግ
ጽህፈት ቤት በሚገኘው በሌላው የአቶ በረከት ቢሮ ውስጥ ነው።(በወቅቱ አቶ በረከት የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሀላፊም
ነበሩና)-በአቶ በረከት የተደረገባቸውን ግምገማ ተከትሎም አቶ ሀይለኪሮስ ወዳልረባ ቦታ ተወርውረው ከነ አካቴያቸው ጠፉ።
ይህን ክስተት፤ በብአዴንና – ህወሐት መካከል ለነበረው፣ ላለውና ወደፊትም ይፈነዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ቁርሾ እንደ አንድ ማስረጃ የተመለከቱት ወገኖች ብዙ ነበሩ።ያም ተባለ ይህ፤ በወቅቱ ብአዴኖች የተሰጣቸውን የስልጣን አርጩሜ(ሙልሙል) ያልተገነዘቡት አቶ ሀይለኪሮስ፤” ቁጭ ብለን የሰቀልነውን-ቆመን ማውረድ አቃተን” እስኪሉ ድረስ ሲያዟቸው በነበሩት በአቶ በረከት እግር ሥር መንበርከክ ግድ ሆኖባቸው ነበር። አቶ በረከት ስምዖን፤የማስታወቂያ ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሀላፊ፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሰብሳቢ…. በአቶ መለስ ዘመን ከፍተኛ ሥልጣን ከሙሉ መብት ጋር የተቀዳጁ የመጀመሪያው ሰው።
በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት፤ይህን ጉዳይ ዛሬ ያስታወስኩት፤ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ተዳፍኖ የቆዬው እሳት የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ የሚፈነዳበት ጫፍ ላይ እንደደረሰ ሲነገር በመስማቴ ነው።
በበኩሌ ሌሎች ሊኖሩ ቢችሉም በግለሰብ ደረጃ በአቶ መለስ ሞት በከፍተኛ ደረጃ ፈተና የተጋረጠባቸው የኢህአዴግ ባለስልጣን አቶ በረከት ናቸው ብዬ አምናለሁ።ይህን የምለው ከአቶ መለስ ጋር ካላቸው እጅግ የጠበቀ ቅርበት አኳያ ከሚፈጠርባቸው የሀዘን ስሜት በመነሳት ብቻ አይደለም። ከዚያ ባላነሰ ሁኔታ አቶ መለስ በነበሩበት ጊዜ ከፍ ዝቅ አድርገው የገመገሟቸው እነ ሀይለኪሮስ፤ ብድራቸውን ለመመለስና ቂማቸውን ለመወጣት በአቶ በረከት ላይ ሊነሱባቸው ይችላሉ የሚል ግምት ስላለኝ ነው።
ምሳሌ ልጥቀስ። በምርጫ 97 የ አዲስ አበባ ውጤት በተገለጸ ማግስት አቶ መለስ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባላትን ሰብስበው በምጸት ፈገግታ፦” የአዲስ አበባን ሕዝብ ምን አድርጋችሁት ነው?” በማለት አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ሲያልቅ ሊኖር ስለሚችለው አስፈሪ ግምገማ ፍንጭ ሰጥተው አለፉ። የተፈራው አልቀረም። ሂደቱ በጡጫና በርግጫ ታግዞ በተጠናቀቀ ማግስት ኢህአዴጎች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ ውስጥ ለግምገማ ተፋጠጡ።
የምርጫው ጉዳይ ዋና አስፈፃሚ ከመሆናቸው አንፃር፤በዚያ ግምገማ ከፍተኛ በትር ያረፈባቸውና ከሌሎች በተለዬ መልኩ በነገር እሳት የተለበለቡት፤ የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር እና መንግስት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምዖን ናቸው። በወቅቱ ከስብሰባው ምንጮች ለመረዳት እንደተቻለው በግምገማው አቶ በረከት ላይ በተለየ መልኩ ጠንክረው የተነሱባቸው ህወሀቶች ነበሩ።
በተለይ በወቅቱ በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በኢህአዴግ መካከል ሲደረግ የነበረው ክርክር በቴሌቪዥንና በራዲዮ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንዲያገኝ መደረጉ፤ የህወሀቶችን ቁጣ በአቶ በረከት ላይ እስኪያነድ ድረስ እንደ ትልቅ ጥፋት የተመዘዘ ነጥብ ነበር። “እሱ ነው በሩን በርግዶ ሰጥቶ ለዚህ ሁሉ ፈተና የዳረገን” ነው ያሉት-ህወሀቶች በቁጣ። በዚያን ሰሞን ፕሮፌሰር መስፍን ፦”እነሱ ገርበብ ያደረጉትን እኛ በርግደነው ገባን” ማለታቸው ትዝ ይለኛል። ልብ በሉ! ለተግባር አልታደልንም እንጂ፤እንኳን በምርጫ ሰሞን በአዘቦቱም ቀን ተቃዋሚዎች በመንግስት ሚዲያዎች መጠቀማቸው፤ ህገ-መንግስታዊ መብት እንጂ፤ የአቶ በረከት የችሮታ ጉዳይ አልነበረም። የሆነ ሆኖ አቶ በረከት ለዚህና በምርጫው ሂደት የኢህአዴግ ጥፋቶች ናቸው ለተባሉ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ዋነኛ ተጠያቂ ተደረጉ።
ጥላ ከለላዬ የሚሏቸው አቶ መለስም በዚያ ግምገማ ከወትሮው በተለዬ መልኩ ቁጣ አዘል የግምገማ ዱላቸውን አሳረፉባቸው ሳይሆን፤ ለሚፈሯቸው ህወሀቶች አሳልፈው ሰጧቸው። የአቶ መለስን ሁኔታና አቋም ሲያዩ አቶ በረከት ከፍተኛ ድንጋጤና ጭንቀት ውስጥ መግባታቸው ተሰምቷል። መቼም የአቶ በረከት ጭንቀት፤-“ አብዮት ልጇን ትበላለች የሚባለው ነገር በኔ ሊደርስብኝ ይሆን?”ከሚል ስጋት የመነጨ እንደሚሆን ምርምር አያስፈልገውም።
ሆኖም ከመበላት ተርፈዋል። ሂሳቸውን ውጠውና ይበልጥ ታማኝነታቸውን አስመስክረው ቦታቸውንና የቀድሞ ተሰሚነታቸውን አስጠብቀው ቀጥለዋል።
በምርጫ 97 ገርበብ አርገው ለሽንፈት ያጋለጡትን ፓርቲያቸውንም፤ በምርጫ 2000 ፤በሩን ሁሉ በመከርቸም በትልቁ ክሰውታል። ከፓርላማ ወንበር 99.6 በመቶውን እስኪያጋብስ ድረስ።
ከዚያስ?
ከዚያ በሁዋላ የስልጣን አኬራ ከብአዴን መንደር የሸሸች ይመስል ነባሮቹ የድርጅቱ አመራሮች ይዘውት ከነበረው ታላላቅ የስልጣን ቦታ በጡረታና በመተካካት ስም ተገፉ። የአቅም ግንባታ ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ዋልዋ ከሦስት አመት በፊት ኢህአዴግ ሰባተኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በአዋሳ ሲያካሂድ በመተካካት ስም “ዘወር በል!” ሲባሉ፤ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የመሰረተ ልማት ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ ለገሰ ደግሞ የዛሬ ዓመት አካባቢ ተሞግሰውና ተሞካሽተው በጡረታ መልክ ከሰሙ።
እነ ህላዊ ዮሴፍንና እነ ገነት ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች ነባር የብአዴን አመራሮች ሥልጣናቸውን ለነ ደመቀ መኮንን እያስረከቡና በአምባሳርነት እየተመደቡ ከዓይን ራቁ። ከህወሀትም እነ ስዩም መስፍን <አትሸኙትም ወይ፤መሄዱ አይደለም ወይ>የሚል ሙዚቃ ተመርጦላቸው 20 ዓመት ከተቀመጡበት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወንበር ተነስተው ወደ ቻይና ተሸኙ። እነ አርከበና እነ አቶ ስብሀትም ወደ ታች ተገፉ።
በአንፃሩ ደኢህአዴጎች በአቶ መለስ ዓይን ሞገስ አገኙ መሰል እነ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ እና እነ አቶ ሬድዋን ሁሴን በተራቸው ወደ ጫፍ እየተሳቡ መጡ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አቶ በረከት አልተነቃነቁም። የማስታወቂያ ሚኒስቴር ወደ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሲለወጥ እንደወትሮው በሚኒስትርነትና እና በመንግስት ቃል አቀባይነት ሹመታቸው ቀጥለዋል። አዎ! አቶ በረከት ከነባር የብአዴንም ሆነ የህወሀት አመራሮች በተለየ መልኩ ሙሉ እምነት ተጥሎባቸው እስከ ህልፈተ -ህይወታቸው ድረስ ከአቶ መለስ ጎን ለረዥም ዓመታት የቆሙ ብቸኛ ሰው ናቸው።
በነዚህ ረዥም ዓመታት አቶ በረከት በአቶ መለስ ጥላ ከለላነት በተደጋጋሚ ከህወሀቶች ጥቃት ተርፈዋል። በአንፃሩ እርሳቸው ህወሀቶችን በተደጋጋሚ ከፍ ዝቅ አድርገው ገምግመዋል፤አዘዋል። በሌላ አነጋገር አቶ መለስ በማሊያቬሊ መንገድ እርስበርስ ለያይተዋቸዋል፤ አቋስለዋቸዋል።
በነ አቶ በረከት እና በህወሀቶች መካከል ያለው ነገር ይህን በመሰለበት ጊዜ ነው ዋናው ሰውዬ ባልተጠበቀ ጊዜና ወቅት እስከ ወዲያኛው ያሸለቡት።
እጅግ ፈፅሞ ያልተጠበቀ አደገኛ አጋጣሚ!
ይህን ተከትለው፤አቶ መለስ ቢለዩም ሥርዓቱ እንደወትሮው እንደሚቀጥል የብአዴኑ አቶ በረከትና የህወሀቱ አቶ ስብሀት እየተፈራረቁ ነግረውናል።እነ አቦይ ለይምሰል ይህን ይበሉ እንጂ በአራቱም አባል ድርጅቶች በተለይ በብአዴን እና በህወሀት መካከል ስር ሰዶ የቆየው ሽኩቻ መፈንዳቱ አይቀሬ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶች እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ እያሉ ነው።
ቂምና የስልጣን ሽኩቻ የፈጠረውን ልዩነት ተከትሎም በአቶ መለስ ተገፍተው የነበሩ በሁለቱም ደርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ነባር አመራሮች ትከሻቸውን ለማሳዬት እንደገና “አለሁ፣አለሁ” ማለት ጀምረዋል።
አውራምባ ታይምስ እንዳስነበበው፤-“መለስ ራሱን ብቻ ሳይሆን፤ ህወሀትንም ነው ገድሎ የሄደው” የሚል ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት አቶ ስብሀት ነጋ፤ ነባር የህወሀት ታጋዮችን የማሰባሰብ ዘመቻ ጀምረዋል። አቶ ስዩም መስፍን የቻይና ቢሯቸውን ቆልፈው አዲስ አበባ ከከተሙ ሰነባበቱ። ይህ ብቻ አይደለም።በኢህአዴግ ስብሰባ ላይ ከነ በረከት ጋር ተቀምጠው የሚወያዩት እነ አባይ ወልዱ፤ ከስብሰባ በሁዋላ ከነ አቦይ ጋር ሆነው ላለመዶለታቸው፤ ምን ማረጋገጫ አለ?።
ከብአዴን ሰፈርም “ጡረታ”ወጥተው የነበሩት እነ አዲሱ ለገሰ “እኛም አለን” እያሉ ነው።ወደ ባህር ማዶ ተገፍተው የነበሩት እነ ህላዊ ዮሴፍ ትከሻቸውን መስበቅ ጀምረዋል። ብአዴኖች፤ “የህወሀት ፈር የለቀቀ የበላይነት በዚህ አጋጣሚ ሊገታ ይገባል” በሚል አቋም ጥርስ ነክሰው መነሳታቸው ይሰማል። ኦህዴድ እና ደኢህዴግ ለጊዜው የሽምግልና ሚና እየተጫዎቱ እንደሆነ ቢሰማም፤ ሁዋላ ላይ አሰላለፋቸውን ሀይል ወዳጋደለበት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
እንደሚታወቀው በአቶ መለስ ሞት ማግስት አቶ በረከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አቶ ሀይለማርያም ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆኑ ቢናገሩም፤ ሹመቱ ሳይፀድቅ በመቅረቱ ኢቲቪ እንደገና አቶ ሀይለማርያምን በቀድሞ ማዕረጋቸው ሲጠራ ቆይቷል። ሹመቱን ለማፅደቅ ተጠርቶ የነበረውም ስብሰባ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጎ እንደነበር አይዘነጋም። አቶ በረከት- አቶ ሀይለማርያምን ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆኑ የገለጹት ህግን ባልጠበቀ መንገድ ነው ተብለው ከህወሀት ከፍተኛ ተቃውሞ አጋጥሟቸው እንደነበርም ይተወቃል። ወይዘሮ አዜብም፦” የመለስ ራዕይ ከማንም በላይ የገባኝ እኔ ነኝ” በማለት ከፍ ያለ ሹመት ለማግኘት ሲላላጡ ሰንብተዋል። በስተመጨረሻም በውጪ አስገዳጅ ተጽዕኖና በሌሎች ምክንያቶች አማራጭ ያጣው ኢህአዴግ የአቶ ሀይለማርያምን ሹመት ለማጽደቅ ተገዷል። ይሁንና የአቶ ሀይለማርያም ሹመት ዋዜማ 37 ጄነራሎች መሾማቸው፤በሹመታቸው ማግስት ደግሞ ስለወደፊቱ የኢትዮጵያ አቅጣጫ እየተናገሩ ያሉት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆኑ፤ እነ አቶ ስብሀትና እነ አቶ በረከት (እየተፈራረቁ) መሆናቸው፤በድርጅቶቹ ውስጥ ተዳፍኖ የቆየው እሳት ከአዲሱ አመራር ሹመት በሁዋላም እየተጋጋመ መቀጠሉን የሚያመላክት ነው። ፍትጊያው ወዴት ያመራል?በምንስ ይቋጫል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።
አንዳንድ ወገኖች አቶ በረከት ባለፉት ዓመታት እስከታች የሚደርስ ጠንካራ ሰንሰለት ስለዘረጉ፤ የሚፈጠረውን ሽኩቻ በአሸናፊነት ሊወጡ እንደሚችሉ ሲናገሩ ይደመጣሉ። ሌሎች ደግሞ የአቶ በረከት ቡድን የፈለገውን ያህል ርቀት ድረስ መዋቅራቸውን ቢዘረጉ፤ አብዛኛው የጦሩ አዛዦች ከህወሀት በመሆናቸውና እነዚህ አዛዦች ክፍፍል ቢፈጠር በገለልተኝነት ይቆማሉ ተብሎ ስለማይታሰብ ፤መጪው ጊዜ ለነ አቶ በረከት በጣም አደገኛ ነው ይላሉ።
ለማንኛውም የሚሆነውን ወደፊት የምናዬው ይሆናል።
ድርጅቶቹ ያረገዙትን የቂም ቁርሾ፦”ጠላትን ደስ አይበለው”በሚል እልህ ለቀናት ሊያዳፍኑት ቢችሉም እንኳ፤ውሎ አድሮ መፈንዳቱ ግን የማይቀር ትንቢት ነው።
No comments:
Post a Comment