Monday, December 31, 2012

365 ቀናት ለሃይማኖት ነጻነት!

365 ቀናት ለሃይማኖት ነጻነት!


የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ መንፈሳዊ ግልጋሎት ይሰጠኛል ብሎ የመሰረተው መጅሊስ የ1987ን የአንዋር መስጊድ ግርግር ተከትሎ ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ገብቶ ለ17 ዓመታት ዘልቋል፡፡ ይህ በህገ መንግስት የተደነገገውን መርህ የሚጥሰው የመንግስት እርምጃ ሙስሊሞችን ለ17 ዓመታት በቁዘማ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ የተጣሰው ሕገ መንግስታዊ መርህ ሳይቃና መንግስት በ2003 የጀመረው አዲስ ጨዋታ ነገሩን ሁሉ ግልጽ አደረገው፡፡ መንግስት የራሱ የግሉ ተቋም ካደረገው እና ከቀዳሚው ስሙ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በተግባር ወደ የኢሕአዴግ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤትነት ከተለወጠው መጅሊስ ጋር በጋራ በመሆን አሕባሽ የተባለ መጤ ቡድን ለመጫን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎችም በወቅቱ አሕባሽ የጽድቅ መንገድ እንደሆነ ሰበኩ፡፡


መንግስት በጥፋት ላይ ጥፋት እየደራረበ በጀመረው በመዝለቅ የተለያዩ እኩይ ድርጊቶችን ሲሰራና ሲያሰራ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህም አንዱ የሕዝበ ሙስሊሙ ተቋም የሆነው አወሊያን ለመጅሊሱ በመስጠት ለአዲሱ መጤ አስተሳሰብ የመጀመሪያ ዳረጎቱን ለገሰው፡፡ መጅሊሱ የአረብኛ መምህራንን በማባረር፣ የመስጊዱን ኢማም ከቦታቸው በማንሳት፣ በአዲሱ አስተሳሰብ ጠመቃ ላይ ያልተገኙትን እና የነቀፉትን ሁሉ በአክራሪነትና ሲከፋም በአሸባሪነት በመፈረጅ ድርጊቱ ገፋበት፡፡ የአወሊያ ተማሪዎች መጅሊሱ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ቀጥሎም ሙስሊሙ ሁሉ በተወካዮቹ አማካኝነት በአገር ውስጥም በውጪም ጭምር መንግስትን ሲማጸን ቆይቷል፡፡ 1. የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት አመራሮች በሙሉ የሕዝበ ሙስሊሙ ውክልና የሌላቸው በመሆኑ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ በነጻነት በሚመረጡ አመራሮች ይተኩልን 2. በመጅሊሱ አማካኝነት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ በግድ እየተጫነ ያለው የአሕባሽ የማጥመቅ ዘመቻ ይቁምልን እና 3. አወሊያ የህዝበ ሙስሊሙ ነጻ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል መጅሊስ እጁን ከአወሊያ ያንሳ፤ በሚል ለመንግስት የቀረቡት ሶስት ጥያቄዎችም ምላሽ ሳያገኙ ጊዜዎች ነጎዱ፡፡ እልህ ፈታኝ ትግልም በሰላማዊ ማእቀፍ ውስጥ በማሰናሰን ከገጠር አነስተኛ ከተሞች እስከ አውረፓ እና ሰሜን አሜሪካ ከተሞች ድረስ ሲከናወን ቆይቷል፡፡ ሕዝባዊ ንቅናቄው በሁሉም ዘርፍ፤ በሁሉም አኳኋን እየተከናወነ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡

ይህ ሰላማዊ ትግል የተጀመረበት ዕለት በመጪው ረቡእ ታህሳስ 24 አንደኛ ዓመቱን ይደፍናል፡፡ ያለፈው አንድ አመት በአገርም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ ወሳኝ ኹነቶች የተስተናገዱበት ነበር፡፡ ታላቅ አገራዊ ንቅናቄ፣ በታሪክ ያልታየ አዲስ ለመብት የተቆርቋሪነት ስሜት፣ በመርህ ላይ የተመሰረት ኢስላማዊ ወንድማማችነት፣ ለመሪ ታዛዥነት፣ ሰላማዊነትና ለሰላም ተቆርቋሪነት ባለፉት 12 ወራት ጎልተው ከወጡ እሴቶቻችን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ እሴቶቻችን ላለፉት 365 ቀናት ከቀን ወደ ቀን ሲያበቡና ሲጎመሩ አይተናቸዋል፡፡ እንደ ሕዝብ ስለ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሲሰጡ የነበሩ አሉታዊ ግምቶችን ሁሉ አፍርሰዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአላህ እርዳታ ቀጥሎ የመሪዎቻችን ፋታ የለሽ ጥረት ወሳኙን ቦታ ይይዛል፡፡

ይህ ለሃይማኖት ነጻነት የተዋደቅንለት ትግል 365 ቀናትን መጓዝ የቻለው ያለምንም ጥረት አይደለም፡፡ ብዙዎች ንቅናቄያችን መጥቶ በቅጽበት የሚያልፍ ጎርፍ ነው ብለው ደምድመው ነበር፡፡ ኢስላማዊ አንድነታችን አሸዋ ላይ የተገነባ ቤት ነው ብለው አስበው ነበር፡፡ ለመሪዎቻችች ያለን አመኔታ የወረት ነው ብለው ያሰቡም ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ግን ሁሉም ከገመቱት ውጪ በመሆን የሰላምን ባንዲራ ይዘን አቀበቱን በአንድነታችን ወጣነው፡፡ ይህ አቀበት ከጠበቅነው በላይ ረዝሞ ብናገኘውም ጉዞውን ለመጨረስ አሁንም በአደባባይ ቃል ኪዳን ተሳስረናል፡፡ ለ365 ቀናት የከፈልነው መስዋእትነት ለማንም ወገን በእምነታችን ጉዳይ ሟች መሆናችንን አሳይተንበታል፡፡ ጠላት ያሻውን ሤራ ቢጎነጉን ከአቋማችን፤ ከእምነታችን ወደ ኋላ እንደማንል አስረግጠን ገልጸንበታል፡፡

አሁን ዞር ብለን 365 ቀናቱን የምናይበት ጊዜ ደርሷል፡፡ ያሳለፍነውን አንድ ግን ረጅምና ፈታኝ የትግል ዓመት እያሰብን የወደፊቱን የትግል ቀለበት የምናጠልቅበት ወቅት አሁን ነው፡፡ ይህን የትግሉን 12 ወራት ጉዞ በማሰብም ‹‹365 ቀናት ለሃይማኖት ነጻነት!›› የሚል መርሐ ድርጊት ለመተግበር ተዘጋጅተናል፡፡ ይህ መርሐ ድርጊታችን ለአራት ሳምንታት በተለያዩ ስያሜዎች እና እርከኖች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን አራቱ ሳምንታትም የየራሳቸው ድርጊቶች ተካተውባቸው ለተግባራዊነት ዝግጁ ሆነዋል፡፡ የመርሐ ድርጊታችን የመጀመሪያ እለት እንዲሆን የተወሰነው የአወሊያ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የኢሕአዴግ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት (መጅሊሱ) የወሰዳቸውን አሳፋሪ እርምጃዎች በመቃወም ድምጻቸውን በት/ቤቱ ቅጽር ማሰማት ከጀመሩበት ከታህሳስ 24 ነው፡፡ በዚህም መሰረት

1ኛ ሳምንት
የአወሊያ ተማሪዎች እና የጥያቄዎቻችን ሳምንት
(ዝምታዉ የተሰበረበት ሳምንት)
ከረቡእ ታህሳስ 24 እስከ ማክሰኞ ታህሳስ 30፣

2ኛ ሳምንት
የኮሚቴዎቻችን፣ የትግሉ ሰማእታት እና የትግሉ ሰለባዎች ሳምንት
ከረቡእ ጥር 1 እስከ ማክሰኞ ጥር 7፣

3ኛ ሳምንት
የሶደቃ እና የአንድነት ሳምንት
ከረቡእ ጥር 8 እስከ ማክሰኞ ጥር 14 እና

4ኛ ሳምንት
የቃልኪዳን ሳምንት
ከረቡእ ጥር 15 እስከ ማክሰኞ ጥር 21
በሚሉ ስያሜዎችና ተግባራት ተደልድለዋል፡፡

መጀመሪያው ሳምንት መርሐ ድርጊት በመጪው ረቡእ የሚጀመር ሲሆን በገጠር፣ በከተማም ሆነ በውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሁሉ ላልሰሙት በማሰማትና አመቱን በደማቅ ትውስታና የትግል ስሜት ለማሳለፍ የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ተዘጋጅተን እንድንጠብቅ እናስታውሳለን፡፡

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment