Thursday, December 20, 2012

ቃላችን አይታጠፍም፤ ወንጀለኞችን እንፋረዳለን


ቃላችን አይታጠፍም፤ ወንጀለኞችን እንፋረዳለን

የሽፍታ ቡድን የፈለገውን ዓይነት ወንጀል ቢሰራ እንኳ አንድ ቀን በሕግ ቁጥጥር ስር ሊውል እንደሚችል ያስባል፡፡ ነገር ግን፤ በመንግስትና በሕግ የተጠለለ ወንጀለኛ ቡድን በህግ ቁጥጥር ስር እንደማይውል ስለሚያስብ አውሬነቱ ለከት የለውም፡፡

በድሃዋ ሐገራችን ከሚገኙ አሰቃቂና ገሀነማዊ ቦታዎች ዋነኛው መሃል አዲስ አበባ የሚገኘው ማዕከላዊ እስር ቤት ነው፡፡ ይህ እስር ቤት የደርግ አብዮት ጠባቂ ‹‹መርማሪዎች›› እስረኞቻቸውን የሚያሰቃዩበት የገሃነም ደጃፍ ነበር፡፡ ዛሬም ይህ ቦታ የስቃይ መንገዱና ዱላው ከመቀነስ ይልቅ ዘመናዊ የስቃይ መሳሪያዎችን ጨምሮ ቀጥሏል፡፡ ከ15 ቀናት በፊት በኮሚቴዎቻችን ላይ ከደረሱት ዘግናኝና ነውረኛ ድርጊቶች ውስጥ እጅግ ጥቂቱን ለመግለጽ ሞክረናል፡፡ ሐገሪቱን እና የሙስሊሙ ወቅታዊ ሁኔታ ለሚከታተሉ ሁሉ በኮሚቴዎቻችን፣ በዱኣቶቻችን፣ በጋዜጠኞቻችንና በአርቲስቶቻችን ወዘተ ላይ የተፈጸሙት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ግፎች ፈጻሚዎችን በሙሉ አንድ በአንድ የምንፋረድ መሆናችን እና መቼም ከሕሊናችን የማይጠፋ ወንጀል መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ ታሪክ ምስክር ነው፡፡
ሠላማዊነቱ ከሐገራችን አልፎ በዓለማቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ከበሬታ ያገኘው እንቅስቃሴያችን ከመነሻው ጀምሮ በሕዝብ የተመረጡ መፍትሄ አፈላላጊዎች አሉት፡፡ ሕዝባችን ጥያቄውን ሲያቀርብ መንግስት በሕሊናው እንደሚያስብ የፍትህ አካላም ሕግ እንደሚያከብሩ በመገመት ነበር፤ ነውም፡፡ ነገር ግን፤ በማዕከላዊ ምርመራ የነበረው ሁኔታ ኮሚቴዎቻችንና ኡስታዞቻችን የሕግ ከለላ ባለው የሽፍታ ቡድን ቁጥጥር ውስጥ የገቡ አስመስሎታል፡፡ ባገኘነው መረጃ መሰረት ‹‹መርማሪ›› ተብዬዎቹ ወንጀለኞች ችሎታቸው ወንጀል መርምሮ ማግኘት ሳይሆን ኢ-ሰብዐዊ እና ኢ-ኢትዮጵያዊ ድብደባዎችን ማድረስ ነው፡፡ የደህንነት ሰዎቹም ኢትዮጵያ ውስጥ በትክክልም ሽብር ለመፍጠር የተደራጀ አካል ቢኖር የሚደሰቱ ናቸው፡፡ እስከ ረመዳን 21 ድረስ በኮሚቴዎቻችን ላይ በተካሄደው ምርመራ ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ለፖሊስ በተጻፈ ደብዳቤ ኮሚቴዎቹ አካላዊና አዋራጅ በሆነ ቅጣት ‹‹እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ሞክረናል ብለው ቃል እንዲሰጡ አስገድዷቸው›› የሚል ደብዳቤ መላኩን አረጋግጠናል፡፡ የማዕከላዊ ሰዎችም ከዚህ ደብዳቤ በኋላ የተካኑበትን ነውረኝነት ማሳየት ጀመሩ፡፡ ጊዜው ሲደርስ ሁሉንም በዝርዝር የምንገልጽ ቢሆንም ስቃዩን በተወሰነ መልኩ ለመግለጽ እንሞክራለን፡፡

• በዚህም መሠረት አንዳንዶቹ ላይ በኮዳ የፈላ ውሃ በመሙላት የዘር ፍሬያቸው ላይ በማንጠልጠል የዘር ፍሬያቸው አብጦ መጸዳጃ ቤት መቀመጥ ተቸግረው ሰንብተዋል፡፡

• በደረሰበት ድብደባ ለከፍተኛ የጀርባ ሕመም የተጋለጠው አንድ እስረኛም ያመመውን ቦታ እየለዩ የሕመሙን አካባቢ በብረትና በዱላ ሲደበድቡ ሰንብተዋል፡፡

• ከኮሚቴዎቻችንና ከኡስታዞቻችን መካከል ጥርሳቸው እስኪነቃነቅ፣ ራሳቸው ስተው እስኪወድቁ የተገረፉና የተደበደቡ አሉ፡፡ ለተከታታይ ቀናት በድብደባና በስቃይ ብዛት ሲጮሁ ድምጻቸው ጠፍቶ ቁርኣን መቅራት ተስኗቸዋል፡፡

• በየድብደባው መሃል የምንልህን እሺ ብለህ ካልፈረምክ ቤተሰብህን ከነልጆችህ ቤታቸውን በእሳት እናጋየዋለን. እናርዳቸዋለን ይሏቸው ነበር፡፡

• ከሁሉ በላይ ኡስታዞቻችን በዚህ ስቃይ መሃል ዓይናቸውን በፎጣ ቢሸፈኑም የሦላት ሰዓት ላለማሳለፍ ብለው ለሶላት ሲቆሙ ‹‹አይናቸው አያይም›› በሚል ትዕቢት ተወጥረው ሱጁድ ማድረጊያቸው ላይ እግራቸውን በማድረግ ጫማቸው ላይ ሱጁድ ለማስደረግ የሞከሩት ጉዳይ መቼም፣ መቼም የማንረሳው ድፍረት ነው፡፡ ‹‹ይሄ ጉዳይ ይረሳል›› ብሎ ማሰብም የዘበት ዘበት ነው፡፡

ማዕከላዊ እስር ቤት አሰራሩ ሁሉ ለስቃይ የታሰበ ነው፡፡ ደረጃው፣ ከፍታ፣ ዝቅታ፣ ውሃ ጉድጓዶች፣ ጎድጓዳ ቦታዎች፣ እንቅፋት፣ ጠባብ መንገድ ወዘተ፡፡ እነዚህን ሁሉ አይናቸውን ጨፍነው በባዶ እግር አሯሩጠዋቸዋል፡፡
አንደኛው የኮሚቴ አባል በድብደባ ከንፈሩ ተሰንጥቆ ኦፐሬሽን በሚያስፈልገው ሁኔታ ላይ ገብቶ ነበር፡፡

ረመዷን መጨረሻውን ‹‹እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ሞክሬአለሁ ብለህ ካልፈረምክ ሰላት አንፈቅድም፤ እረፍት የለም፤ ስቃይ ነው›› እየተባሉ ታመው፣ ‹ሐኪም ታሟል ይረፍ› እያለ ለሳምንታት በጨለማና በቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ ያለ ፉጡርና ሱሁር በረሃብ አለንጋ የሚያሰቃዩኣቸው አንሶ በደረቅ ለሊት ለሰዓታት ያለ ምንም እረፍት ስፖርት ያሰሯቸው ነበር፡፡
በማሽን ሰውነታቸው እየተጨመቀ እንኳ በዚህ ስቃይ ውስጥ ነፍሳቸው ጉሮሯቸው ላይ ደርሳ እነሱ ግን የሚናገሩትን በካሜራ ቀርፆ ለማስቀረት ሲሞክሩ ነበር፡፡ ወዘተ… ወዘተ…

በመጨረሻም

ትናንት የነበሩ የደርግ አብዮት ጠባቂዎች ጊዜው ደርሶ ለፍርድ እንደቀረቡ ሁሉ ኮሚቴዎቻችንን ሲያሰቃዩ የሰነበቱትንም ሁሉ እንደምንፋረድ እንገልጻለን፡፡ ይህ ደግሞ ቃላችን ነው፡፡

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment