Tuesday, December 18, 2012

ፍትህ የማግኘትን ተስፋ ያዳፈነው የፍ/ቤት ውሎ

ፍትህ የማግኘትን ተስፋ ያዳፈነው የፍ/ቤት ውሎ

ፍ/ቤቱ ብዙዎቹን መቃወሚያዎች ውድቅ አድርጓቸዋል

‹‹ወንጀል ተፈጽሞብኛል እንጂ ወንጀል አልፈጸምኩም››ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው

ማለዳ ላይ የተሰየመው የልደታ ፍ/ቤት አቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሀሰት ክስ ተንተርሶ የመሪዎቻችንን እና ወንድሞቻችንን ጠበቆች መቃወሚያ እንዲሁም የአቃቤ ሕጉን የመቃወሚያ መቃወሚያ አድምጦ ውሳኔ ለማሳለፍ ነበር ቀጠሮ የሰጠው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ቀጠሮ ፍ/ቤቱ ለውሳኔ የሚረዱኝ የመቃወሚያ ግልባጮች በጽሁፍ ተገልብጠው አልደረሱኝም በሚል ምክንያት ውሳኔውን መስጠት ሳይችል ቀርቶ ነበር ቀጠሮው ወደ ታህሳስ 8 የዞረው፡፡ ሆኖም በእለቱ ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ ሁኔታ መሪዎቻችን እና ወንድሞቻችን ፍ/ቤት እንዳይቀርቡ ተደርጓል፡፡
ፍ/ቤቱ ከጠበቆች በኩል የቀረበለትን መሰረታዊ የሕግ መራከሪያዎች ተንተርሶ ተገቢውን ብይን ይሰጥ ይሆናል የሚል ተስፋ በአንድ አንዶች ዘንድ አድሮ የነበረ ቢሆንም ያ እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ የመሪዎቻችንን እና ወንድሞቻችንን ጠበቆች መቃወሚያ ዋነኛ ማጠንጠኛ የነበሩና የአቃቤ ሕግ ክስ ውድቅ እንዲሆን አልያም ሕገ መንግስታዊ ትርጓሜ የሚያሻው በመሆኑ ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ ከዚህም አልፎ ክሱን ይህ ፍ/ቤት ሊመለከተው አይገባም የሚሉት ሐሳቦችን ፍ/ቤቱ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ሳይቀበላቸው ቀርቷል፡፡ ጠበቆች የአገሪቱን ሕገ መንግስት እና ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶች በመጥቀስ ጭምር ባቀረቡት መከራከሪያ ክሱም ሆነ ክሱ የተመሰረተበት የጸረ ሽብር ሕግ ከሕገ መንግስቱ በተጻራሪ አቅጣጫ የቆሙ መሆናቸውን በጉልህ በማሳየት የክሱን ሕገ ወጥነት አስቀምጠው ነበር፡፡ ቀደም ሲል በነበሩት ችሎቶች ለጠበቆቹ መቃወሚያ ሌላ መቃወሚያ ያቀረበው የአቃቤ ሕግ ቡድን በአይን በሚታይ መልኩ የሰጠው ምላሽ ተመጣጣኝ ያልነበረና በሽፍንፍን የታለፈ ነበር፡፡ ፍ/ቤቱ ግን እንዚህን ሁሉ ክግንዛቤ ሳያስገባ ክሱ ሕገ መንግስታዊ ትርጓሚ የሚያስነሳ አይደለም፣ የጸረ ሽብር ሕጉም ከሕገ መንግስቱ ጋር አይቃረንም እና ይህ ፍ/ቤትም ጉዳዩን ማየት ይችላል የሚል ብይን በትላንትናው እለት አሳልፏል፡፡

በሌላ በኩል ጠበቆች በአንድ ወንጀል ሁለት ጊዜ ክስ በሚል ባቀረቡት መቃወሚያ ማለትም የጸረሽብር አዋጅ አንቀጽ 3 (በቀጥታ የሽብር ተግባር መፈጸም) ተጠቅሶ እንዲሁም አንቀጽ 4 (የሽብር ድርጊት እንዲፈጸም ማነሳሳት) ተጠቅሶ በአንድነት መከሰሳቸው ተገቢ ስላልሆነ በሚል ክሱ በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 3 (በቀጥታ የሽብር ተግባር መፈጸም) በሚለው እንዲቀጥል ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ በሚል የተጠቀሰው ክስ በሽብረ ተግባር በሚለው ውስጥ መጠቃለል የሚችል በመሆኑ ክሱ በዚያው እንዲሸጋሸግ የተወሰነ ሲሆን ቀኑና ወሩ ባልጠጠቀሰ ከ2001 ጀምሮ በህቡእ በመደራጀት የሚለው የአቃቤ ሕግ ክስ የጸረ ሽብር ሕጉም የወጣው በዚሁ 2001 ዓመት በመሆኑ ሕጉ ተመልሶ ወደ ኋላ የማይሰራ ስለሆነ ክሱ ውድቅ ይደረግ የሚለው መከራከሪያም በፍ/ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡

23ኛ ተከሳሽ አብዱራዛቅ አክመል የአዕምሮ በሽተኛ በመሆኑ ክሱ እንዲቋረጥ ጠበቆች ጠይቀው የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ሆኖም ወንጀሉ በተፈጸመ ጊዜ የአዕምሮ በሽተኛ ስለመሆኑ ከአማኑኤል ሆስፒታል እንዲረጋገጥና ክሱም ተነጥሎ እንዲታይ ፍርድ ቤቱ አዟል። ከሃያ ስምነቱ ተከሳሾችና ወንድሞቻችን በተጨማሪ የተከሰሱት ሁለቱ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መኪና አውሳቹሀል ተብለው ሊከሰሱ አይገባም ተብሎ በጠበቆች የቀረበው መቃወሚያም እንዲሁ በፍ/ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ጠበቆች ካቀረቧቸው ስምንት መቃወሚያዎች ፍ/ቤቱ ሁለቱን ብቻ ያውም ሽፍንፍን ባለ መልኩ ተቀብሏል፡፡ ሌሎቹን ግን ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡

ሌላው የ28ኛ ተከሳሽ ወሮ ሀቢባ ክስ ተነጥሎ እንዲታይ በጠበቃቸው አማካኝነት የቀረበውን መቃወሚያም ፍርድ ቤቱ አልተቀበልኩትም ብሏል፡፡ ፍ/ቤቱ እነዚህ ውሳኔዎችን በመንተራስ ክሱ እንዲሻሻል የጠየቀ ሲሆን ጠበቆች በበኩላቸው አቃቤ ህግ ክሱን አሻሽሎ እስከሚያመጣ ተከሳሾች በዋስትና መብት ይውጡ ብለው ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ሊቀበለው አልፈቀደም፡፡

በቀጣይነት በችሎቱ የተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል ወዲያው እንዲሰማ ቢጠይቅም ጠበቆች ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱ የለወጠውን እና ያሻሻላቸውን ነገሮች ስላልተረዱ እንድናስረዳቸው እድል ይሰጠን ብለው የጠየቁ ሲሆን፤ 15 ደቂቃ ያህል እድል ተሰጥቷቸውም ለመሪዎቻችንና ወንድሞቻችን የክሱን ሽራፊ ለውጥ አስረድተዋል፡፡ በቀጣይነትም ፍርድ ቤቱ ‹‹የተከሰስክበትን ድርጊት ፈጽመሀል? ጥፋተኛ ነህ ?›› በማለት ሁሉንም በየተራ ለጠየቃቸው ጥያቄ ድርጊቱን አልፈጸምኩም፣ ጥፈተኛ አይደለሁም፣ በህገ-መንግስት የተሰጠኝን መብት ነው የጠየቅኩት እንጂ ወንጀል አልፈጸምኩም የሚሉና መሰል መልሶችን የሠጡ ሲሆን ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው ‹‹ወንጀል ተፈጽሞብኛል እንጂ ወንጀል አልፈጸምኩም›› በማለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ብዙዎቹ ወንድሞቻችንም ሕገ መንግስቱ ከፈቀደላቸው ውጪ በምንም ዓይነት ወንጀል ተሰማርተው እንዳልነበርና ሕጉ የሰጣቸውን መብት እንደጠየቁ በመግለጽ ነገም ቢሆን መብታቸውን ከመጠየቅ ወደ ኋላ እንደማይሉ ለፍ/ቤቱ በመግለጽ ሞራላዊ ልእልናቸውን አሳይተዋል፡፡

ፍ/ቤቱ አቃቤ ሕግ ያሉትን የሰው ማስረጃዎች ከጥር 14 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 10 የስራ ቀናት በምስክርነት ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን ለዚሁ ምስክርነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችም በአሁኑ ወቅት የምስክርነት ስልጠና ላይ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል በትላንትናው የችሎት ውሎ ከፊል የመሪዎቻችን ቤተሰቦች ችሎቱን እንዲታደሙ የተፈቀደ ቢሆንም ሌሎች ቤተሰቦችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለሰቦች ግን ወደ ችሎት ከመግባት በፖሊስ ታቅበው ነበር፡፡ በፍ/ቤቱ ውስጥ ክፍት ወንበሮች በብዛት የነበሩ ሲሆን በተለምዶ የሚቀርበው ቦታ የለም መልስም ብዙ አሳማኝ እንዳልሆነ በድጋሚ ተረጋግጧል፡፡ ከፍ/ቤቱ ግቢ ውጪም የፌደራል ፖሊስ የልደታ መተላለፊያ መንገዶችን አጥሮ ሙስሊም ነው ብሎ የጠረጠረውን ሁሉ ከመንገድ ሲመልስ ታይቷል፡፡ በቁጥር ከ40 የሚበልጡ ሙስሊሞችንም (ብዙዎቹ ሴቶች) አፍሶ መውሰዱን እማኞች ገልጸዋል፡፡

በመሪዎቻችንም ላይ ሆነ በወንድሞቻችን ላይ የተመሰረተው ክስ መቼም ቢሆን ተቀባይነት እንደማይኖረው ዛሬም ለመግለጽ የምንወድ ሲሆን የሀሰት እና የተቀነባበረ ድራማ መሪዎቻችንን ጥፋተኛና አሸባሪ ለማስባል የሚደረገው ሩጫ በኢትዮጵያ የእስልምናን ታሪክ ካለማወቅ የሚመነጭ ጭፍን አመለካከት በመሆኑ ክሱ ውድቅ ተደርጎ መሪዎቻችን በነጻ እንዲሰናበቱ ዛሬም እንጠይቃለን፡፡ መሪዎቻችንን አሸባሪ በማለት ውስጥ የመረጣቸውን የኢትዮጵያ ሙስሊም ሕብረተሰብ በሙሉ አሸባሪ ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግስታዊ የእምነት ነጻነት መብትን መጠየቅ ፈጽሞ ወንጀለኛም አሸባሪም አያስብልም፡፡

አላሁ አክበር!

1 comment:

  1. ashebari tebalum altebalu mangnawem sew yeemenet netsanetu metebek alebet tegelachen le Islam new tegelachen yeemenet netsanet endinor new lemanegnawem zega tegelachen yehelewena teyake new ye identity teyake emenete eskaltekebere hege mengest eskaltekebere hege yebelay eskalhone ager endet selam tagegnalech?

    ReplyDelete