በለቅሶና በዱአ የታጀበው ታላቁ አገር አቀፍ የጁሙዓ ተቃውሞ!!!
‹‹አማኞች አንዱ ለአንዱ ልክ ግድግዳ ላይ እንደተደረደሩ ጡቦች ናቸው፤ አንደኛው ሌላውን ያጠናክረዋል!›› (ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ)
አላሁ አክበር! የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አንድነት ዛሬም ፍንክች የማይል ጠንካራ ግንብ መሆኑን አስመስክሮ ዋለ! መውሊድን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም እርስ በርስ ሙስሊሙን ለመከፋፈል እና ለማጣላት ያሰበው መንግጅሊስ ተንኮል ዛሬም በድጋሚ ፉርሽ ሆነ! በረዥሙ ትግላችን ያሳለፍናቸው በርካታ ጁሙአዎች በደመቀ ስነ ስርአት እየተከናወኑ ያለፉ ቢሆንም ጠለቅ ያለ ስሜት እና አንድነት የሚስተዋልባቸውና ከትውስታ እስከመጨረሻው የማይፋቁ ጁሙአዎች ደግሞ ከሌሎቹ ለየት ብለው ተንጸባርቀው ያልፋሉ፡፡ ትዝታቸውን ለረዥም ጊዜ ይጥላሉ፡፡ የዛሬዋ ጁሙአ ከመሰል ታዋሽ ጁሙአዎች አንዷ ነበረች፡፡ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በተለያዩ የተቃውሞ አይነቶች ያለፈው የዛሬው ጁሙአ በጣም ለየት ያለ ስሜት በህብረተሰቡ ዘንድ አሳድሯል፡፡ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሀይማኖት ተከታይ ወገኖቻችንን የጥምቀት በአል ዝግጅት ታሳቢ በማድረግ የተቃውሞ ቦታው ከአንዋር ወደ በኒ ሰፈር (ኑር መስጂድ) የተቀየረውን የዛሬውን ተቃውሞ ለመቀላቀል ሙስሊሙ ከአዲስ አበባ የተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ፒያሳ መጉረፍ የጀመረው ገና በጠዋቱ ነው፡፡ የተጠራው የሰደቃ ፕሮግራም እንደመሆኑ ሁሉም በኪሱ ለሰደቃ ያዘጋጃትን አንድ አንድ ብር ወንድማማችነቱን ሊገልጽባት ከቋጠራት የብስኩትና ተምር ስንቅ ጋር አዳብሎ ወደመስጊድ ተመመ! በኑር መስጊድ ሰኔ ውስጥ ተዘጋጅቶ በነበረው የሶደቃና አንድነት ፕሮግራም ለፕሮግራሙ የተዘጋጁትን መኪና ሙሉ ኩኪሶች ፖሊስ መውረሱ ይታወሳል፡፡ ዛሬ ቃሊቲ የሚገኘው ወንድማችን ሷቢር በእለቱ ‹‹ፖሊሶች ኩኪሱን መልሱልን፤ ኩኪሱን ልንበላው እንጂ ልናፈነዳው ዐይደለም›› ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ ዛሬም አፎቻቸው ባይንቀሳቀሱም የሁሉም ሰጋጆች ፊት ድምጽ አውጥቶ ይናገር ነበር - ‹‹የሰደቃ ፕሮግራማችንን እንደቀድሞው በሬ እና ኩኪስ በመቀማት ማደናቀፍ አይታሰብም›› እያለ! የሰዉ ቁጥር እጅግ በጣም ብዙ ነበር፡፡ ብዙዎች ‹‹ኑር መስጊድ በታሪኩ እንዲህ ያለ የሰው ቁጥር አስተናግዶ አያውቅም›› ሲሉ እንዲገልጹት አስገድዷቸዋል፡፡ ከመውሊድ መቃረብ ጋር ተስታኮ የሚፈርስ አንድነት እና የሚፈጠር ክፍፍል ካሁን በኋላ የማይሰራ መሆኑን ለማሳየት ከዚህ በላይ ማስረጃ የሚኖር አይመስልም፡፡
ሁሉም በአቅራቢያው ላሉት ችግረኞች ለሰደቃ የተዘጋጀውን አንድ አንድ ብር ከጁሙአ ሰላት በፊት እየሰጠ በመስጊዱ ውስጥና ዙሪያው ተሰባስቧል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ዛሬ በነፍስ ወከፍ የሠጠው አንድ አንድ ብር በሙሉ ቢደመር የሚመጣው ውጤት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ በፕራግራሞቹ የተገኙ ሰዎችን ቁጥር በማየት መገመት አያዳግትም፡፡ ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ የሰደቃ ፕሮግራሞች የገንዘብ ምንጭ ህብረተሰቡ ብቻ መሆኑን አይቶ በመመስከር የመንግስትን ውንጀላ ውድቅ ማድረግ ይቻላል፡፡ ታዋቂው ዳኢ ኡስታዝ መንሱር ከሰላት በፊትም ትምህርት ሰጥቷል፡፡ ኡስታዝ መንሱር ያስተላለፈው መልእክት ብዙዎችን ያስደመመ ነበር፡፡ ሙስሊም ወጣቶች ኢስላማዊ አንድነትን በመገንባት፣ ፍቅር በመፍጠር እና ለዲናቸው በመልፋት እያሳዩ ያለውን ተነሳሽነት አወድሷል፡፡ ለሙስሊም ወጣቶች መዋደድና መተሳሰብ አንገብጋቢ ስለመሆኑም ተናግሯል፡፡
ከጁሙአ ሶላት ማብቃት በኋላ ህዝበ ሙስሊሙ ለአምስት ደቂቃ ያክል እጅ ለእጅ በመያያዝ መውሊድ እንደማይከፋፍለው አረጋግጧል - አመት ሙሉ ሊከፋፍሉት ሲሞክሩ ለነበሩት አካላት ተስፋ አስቆራጭ መልሱን ሰጥቷል፡፡ በማስከተልም በለቅሶ የታጀበ ዱአ ተደርጓል፡፡ በእንባ የራሱ አይኖች በበደል ከተሰበሩ፣ በወኔና እልሕ ከሚንተገተጉ ልቦች የተቀበሉትን መልእክት አድርሰዋል፡፡ እጆች ወደ አላህ ተዘርግተዋል፡፡
‹‹አላህ የተዘረጉ እጆችን ባዶ መመለስ ያፍራል!›› (ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ)
ሁሉም ሙስሊም ለሰደቃ ያመጣቸውን ብስኩቶችና ተምሮች እየተካፈለ ሲመገብ ባለፈው አመት ፍቅሩን፣ አንድነቱን፣ ድሉንና በደሉን አብሮ እንደተካፈለ ሁሉ የማሳረጊያ ድሉንም አብሮ የሚካፈልበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ እያሰበ፣ ለራሱም ቃል እየገባ ነበር! ሁሉም ተቃውሞውን ፈጽሞ በሰላም ወደቤት ሲመለስ ደስታ እየተሰማው፣ ጭንቁንም እያቃለለ ነበር፤ በእውነትም ምርጥ ጁሙአ!
በመንግስት ተደጋጋሚ ግፍ ሲደርስባት የቆየችው ደሴ ከተማ ደግሞ ዛሬ ለየት ያለ ተቃውሞ አስተናግዳለች፡፡ ለትጥቅ ትግል የተዘጋጁ የሚመስሉት ታጣቂ ፌደራሎቿ እና አድማ በታኞቿ በየሳምንቱ ራሱን ከሚቀያይረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር ሊላመዱ ያልቻሉ ሆነው ውለዋል፡፡ አህባሽ ኢማሞች የተሾሙባቸው የደሴ መስጊዶች ዛሬ ጭር ብለው የዋሉ ሲሆን ከነጭራሹ ተቆልፈው የዋሉ መስጊዶችም እንደነበሩ የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ በአሬራ፣ በፔፕሲ፣ በሜጠሮ ጎሮ እና በጠልሃ መስጊዶች እጅግ በጣም ብዙ ሰው የሰገደባቸው ሲሆን አንጋፋዎቹ ኢማሞች ተባርረው የመንግስት ኢማሞች የተተኩባቸው አረብ ገንዳ፣ ሸዋበር፣ ፉርቃን እና ዳዌ መስጊዶች ጭር ብለው ውለዋል፡፡ በእነዚህ መስጊዶች ከ5 እና 10 የማይበልጡ ሰዎችና መስጊዶቹን ከከበቡት ታጣቂ ሀይሎች በስተቀር የተገኘ አልነበረም፡፡ በዛሬው ተቃውሞ ደሴዎች መንግስት እያደረገ ያለው የመስጊድ ነጠቃ ዘመቻ ሊሰራ እንደማይችል እና የመንግስት ኢማሞች በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኙበት ቀዳዳ እንደማይኖር ጠንካራ ድምጽ አልባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በአባ ጂፋሯ ጅማ ከተማም እንዲሁ በፈትህ መስጊድ ከፍተኛ ተቃውሞ ተደርጎ ነበር የዋለው፡፡ ምንም እንኳን ሰዉን ለማስፈራራት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች መስጊዱን ከብበው የቆዩ ቢሆንም ሰላማዊው የጅማ ማህበረሰብ ግን ለሁከት አንዳችም ፍላጎት እንደሌለውና ሰላማዊ ተቃውሞው የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄ ሳይመለስ ሊቆም እንደማይችል ያለጥርጥር አረጋግጦ አልፏል፡፡ በዚያው በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ ጃሚአል ሐቢብ መስጊድም እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞ ተደርጎ መዋሉ የተዘገበ ሲሆን በሻሸመኔ እና መቱ ከተሞች ላይ የነበው ተቃውሞም እንዲሁ እጅብ በርካታ ሰዎች የተገኙበት እና በጣምም የደመቀ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በደቡቧ የወልቅጤ ከተማ የሶደቃና የዱአ ፕሮግራም ተካሄዷል፡፡ መፈክሮችም ከፍ ብለው ተሰምተዋለወ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በግዳጅ የኢማም ለውጥ ምክንያት ለአራት ሳምንታት ያህል የጁምአ ሰላት ሳይሰገድባት የቆየችው የመቅደላ ወረዳዋ ማሻ ከተማ ዛሬ በመንግስት የተሾመው ኢማም ተነስቶ ሕዝቡ በመረጣቸው ኢማም አማካኝነት የጁምሰ ሰላት በጋራ መከናወኑ ተሰምቷል፡፡
አዎን! ዛሬም ሙስሊሙን ለመከፋፈል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አንድ በአንድ እየከሸፉና እየረገፉ ናቸው፡፡ በልማትና አገር ግንባታ ፋንታ አላስፈላጊና አጥፊ ተግባር ላይ ጊዜውን እየፈጀ፣ ህዝቦቹንም እያሰቃየ ያለው መንግስት ግን ከስህተቱ ለመማር ገና ፈቃደኛ እስኪሆን ሚሊዮኖች እየጠበቁት ይገኛል፡፡ አሁንም ተቃውሟችን ድምጻችን እስከሚሰማ፣ እስከሚደመጥም ይቀጥላል!
በመጨረሻም በቀጣይ ቀናት የሚደረጉ ተጨማሪ የሰደቃ ስራዎችን የምናሳውቅ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment